በዞኑ ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የተለያዩ ችግኞች ይተከላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የተለያዩ ችግኞች ይተከላሉ
ደብረ ማርቆስ ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን በመጪው ክረምት ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ የተለያዩ ችግኞች እንደሚተከሉ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ቡድን መሪ አቶ ንጉሴ ሽመልስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን አጠናከሮ በማስቀጠል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተሰራ ነው።
በዚህም በመጪው ክረምት ለሚካሄደው ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚውል ከ264 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በክረምቱ ወቅት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ ችግኞችን ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል የኮሶ፣ ግራር፣ ወይራ ፣ ጌሾ ፣ ብሳና ፣ ዋንዛ ፣ ባህር ዛፍ ፣ የጽድና ሌሎች የደንና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።
በተጨማሪም የሙዝ፣ አቮካዶ ፣ ማንጎ ፣ ፓፓያና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች መኖራቸውን ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅትም አርሶ አደሩ የሚተከሉ ችግኞች ጠቀሜታን በመገንዘቡ በግልና በማህበር ችግኞችን ማዘጋጀት መጀመሩንም ገልፀዋል።
በዞኑ የአዋበል ወረዳ የወጀል ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መልሰው ገናነው እንደገለጹት፤ የችግኝ ተከላው የአካባቢ መራቆትን ከመታደግ ባሻገር የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ እያስቻለን ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ጥቅሙን በመገንዘባቸው በክረምቱ በግልና በህብረት ችግኞች ለመትከል መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገሩት።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ውጤታማ እንዲሆኑ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ በዞኑ የአነደድ ወረዳ የጉዳለማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተሻለ ጌታሁን ናቸው።
ካለፉት ዓመታት ባገኙት ልምድ በመነሳትም በክረምቱ የሚተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የጽደቀት መጠናቸው እንዲጨምር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።