ቀጥታ፡

ሞሮኮ ከሃይቲ፤ ደቡብ አፍሪካ ከኮሪያ ሪፐብሊክ የዓለም ዋንጫ ወሳኝ የምድብ ጨዋታዎች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ):- የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ።

ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ሞሮኮ ከሃይቲ በአትላንታ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ ያገኘችው ሞሮኮ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ሞሮኮ ካሸነፈች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ትገባለች፤ በአቻ ወይም በሽንፈት ውጤት ደግሞ በምርጥ ሶስተኛነት የማለፍ ዕድል ይኖራታል።

ከውድድሩ መሰናበቷ የተረጋገጠው ሃይቲ የመጨረሻ ጨዋታዋን ታደርጋለች።

በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ስኮትላንድ ከብራዚል በሚያሚ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።




ስኮትላንድ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ፣ ብራዚል በአራት ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዘዋል።

ማሸነፍ ስኮትላንድን በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ያስገባታል። አቻ መውጣት በሂሳባዊ ስሌት በምርጥ ሶስተኝነት ሊያሳልፋት ይችላል።

ብራዚል ካሸነፈች ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቷን ታረጋግጣለች፤ አቻ መውጣት ወይም መሸነፍም ቢሆን ወደ ቀጣዩ ዙር ሊያሳልፋት ይችላል።

በተያያዘም የምድብ አንድ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

በሞንቴሬይ ስታዲየም ደቡብ አፍሪካ ከኮሪያ ሪፐብሊክ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ደቡብ አፍሪካ በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዛለች። ኮሪያ ሪፐብሊክ በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ደቡብ አፍሪካ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ያላት ብቸኛ እድል የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ብቻ ነው።

በአንጻሩ ኮሪያ ሪፐብሊክ ማሸነፍ ቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ያስገባታል። የአቻ ውጤት በምርጥ ሶስተኝነት ሊያሳልፋት የሚችልበት እድል አለ።

በዚሁ ምድብ ቼክ ሪፐብሊክ ከሜክሲኮ በተመሳሳይ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በሜክሶኮ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።




ከአዘጋጆቹ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሜክሲኮ ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቷ ይታወቃል። ካሸነፈች ውይም አቻ ከወጣች የምድቡ መሪ ሆና ታጠናቅቃለች።

ቼክ ሪፐብሊክ በአንድ ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋዋን ለማለምለም ያላት ብቸኛው እድል ማሸነፍ ብቻ ነው።

በምድብ ሁለት ስዊዘርላንድ ከካናዳ በቢሲ ፕሌስ ስታዲየም ምሽት አራት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ካናዳ እና ስዊዘርላንድ በተመሳሳይ አራት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።

አሸናፊው ሀገር በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ይገባል። የአቻ ውጤት ሁለቱንም ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳልፋል።

ሽንፈት የሚያስተናግደው ቡድን ምርጥ ሶስተኛ ሆኖ የማለፍ እድል አለው።

በዚሁ ምድብ ቦሲኒያ እና ሄርዞጎቪና ከኳታር ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ በሲያትል ስታዲየም ይጫወታሉ።

ቦሲኒያና ሄርዞጎቪናና ኳታር በተመሳሳይ አንድ ነጥብ በግብ ልዩነት ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የሀገራቱ ብቸኛ የማለፍ እድል ማሸነፍ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም