ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ብልፅግናን የሚያረጋግጥ አዲስ የከተማ ልማት ምዕራፍ ውስጥ ገብታለች

አዲስ አበባ፤ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ብልፅግናን የሚያረጋግጥ አዲስ የከተማ ልማት ምዕራፍ ውስጥ መግባቷን በገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ትዕግሥት ፍስሀ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት “ከለውጥ ወደ ዘላቂ ሽግግር” በሚል መሪ ቃል የ“ኢትዮጵያ ታከናውናለች” ጉባኤ በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።

በገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ትዕግሥት ፍስሀ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ አዲስ የከተማ ልማት ምዕራፍ ውስጥ ገብታለች።

ትኩረቱም ከተሞችን ማስፋፋት ላይ ብቻ ሳይሆን ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንዲሁም ምቹ፣ ተወዳዳሪ፣ ሁሉን አቀፍና ዘመናዊ ማድረግ ነው ብለዋል።

አማካሪዋ አክለውም፥ ይህም ከተሞች ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለጋራ ብልፅግና ቀጣይ ሞተር እንዲሆኑ የማድረግ ውጥን እንዳለውም አብራርተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተሞች ከሀገር ውስጥ ገቢ አብላጫውን እንደሚያመነጩ ገልፀዋል።

ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚ፣ከመንግስት መር ኢኮኖሚ ወደ ገበያ መር ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በማድረግ በርካታ ለውጦች እንዲመዘገቡ መቻሉን ጠቅሰዋል።

የአንድን ውጤታማ ከተማ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት፣ ቀልጣፋ መሰረተ-ልማት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠር ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልፀው፥ ይህም ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ የተገነቡትን የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ ፓርኮች፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ እና መሰረተ ልማት ግንባታዎች በማሳያነት ጠቅሰዋል።

መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የተጀመረው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መስፋፋት አበረታች ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ከስራ እድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ገላን ጉራ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል እየፈጠረ ያለ ኢንዱስትሪ መሆኑ ገልፀዋል።

በዚህም ለሀገር ውስጥ አምራቾች የተለያዩ የማበረታቻ ድጋፎች በማድረግ ተኪ ምርት ላይ በትኩረት እንዲሠሩ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት መቻሉን አንስተዋል።

አዲሱ የልማት ምዕራፍ ጠንካራ የገጠርና የከተማ ሽግግር መፍጠር መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ሁሉን አቀፍ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ጠንካራ መሠረት ይሆናል ብለዋል።

በተሠሩ ሁሉን አቀፍ የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ የሚያስችሉ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙም አማካሪዋ ጨምረው ገልፀዋል።

እንዲሁም ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ በሚያስችል መልኩ የልማት ሥራዎቹ ተጠናክረው መቀጠላቸውን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም