ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ማንሠራራት ጠንካራ መሠረት እየገነባች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ማንሠራራት ጠንካራ መሠረት እየገነባች ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ማንሠራራት በመሠረተ ልማት፣ በተቋማዊ አቅምና በዲጂታል ክህሎት ጠንካራ መሠረት እየገነባች እንደምትገኝ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዲጂታል አማካሪ ሚሪያም ሰዒድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት “ከለውጥ ወደ ዘላቂ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ የ“ኢትዮጵያ ታከናውናለች” ጉባኤ ተካሂዷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዲጂታል አማካሪ ሚሪያም ሰዒድ፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ተበታትነው የቆዩ አሠራሮችን በዲጂታል ማንነት፣በክፍያ እና በዳታ ልውውጥ የተቀናጁ የኢኮኖሚ መዋቅሮች ውስጥ በማስገባት ለሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ምቹ የሆነ ምህዳር እየገነባች መሆኑን አመልክተዋል።
የመንግሥት አገልግሎቶችን በማገናኘት እንዲሁም የሀገር በቀል አቅምን በጋራ በማሳደግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኢኮኖሚያዊ እድገት በምርት፣ በወጪ ንግድ እና በኢንቨስትመንት አቅሞች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ወደ ተሻለ ዕድገት ለማሸጋገር የዲጂታል አሠራሮች መጠናከር ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ የዲጂታል ስትራቴጂዎች ትግበራ በማዕድን፣ በግብርና፣ በከተሞች እና በመሠረተ ልማት ላይ ሰፊ በሆነ የኢኮኖሚ ሽግግር ውስጥ በስፋት እያሳየች መሆኑን ገልጸዋል።
የዲጂታል አገልግሎትን የሚያፋጥኑ መሠረተ ልማቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መሠራቱ የክፍያ ሥርዓቶች በኢኮኖሚው ውስጥ የምዝገባ፣ የግብይት እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ይህንኑ የዲጂታል ሪፎርም ወደ ምርታማነት ለመቀየር ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ የሆኑትን የፋይናንስ ችግር፣የባለሙያዎች አቅም ውስንነት መፍታት ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።
ሀገሪቱ ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችል ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራትም የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን ተናግረዋል።
በአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ በርካታ ዜጎችን የማብቃት ሥራ በስፋት እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል።
ኢትዮጵያ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማትና ትግበራ የሚሆን ተቋማዊ፣ የሰው ሃይልና የቴክኖሎጂ አቅም ላይ ትኩረት መስጠቷንም አንስተዋል።
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ፣በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን፣ ሥርዓት ፈጣሪዎችን ለማሰልጠን እና ምርምርን ከተግባር ጋር ለማገናኘት የተነደፈ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።