ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት ወደ ተጨባጭ ብሔራዊ ዕድገት አቅም እየቀየረች ነው- ኢንጂነር ሐና ብርሃኑ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት ወደ ተጨባጭ ብሔራዊ ዕድገት አቅም እየቀየረች መሆኑን የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሐና ብርሃኑ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት፣ “ከለውጥ ወደ ዘላቂ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ የ“ኢትዮጵያ ታከናውናለች” ሀገራዊ ጉባኤ በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሐና ብርሃኑ በመድረኩ የዘርፉን የትራንስፎርሜሽን ጉዞ አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢንጂነር ሐና በማብራሪያቸው፤ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የማዕድን ሀብት በተቀናጀ መልክ ወደ ተጨባጭ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት አቅም እየቀየረች መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገሪቱ የማዕድን ዘርፍ ቀደም ሲል ከነበረበት ደካማ አፈጻጸምና ተግዳሮቶች ተነስቶ፣ በአሁኑ ወቅት ከኢኮኖሚ ዕድገት ስትራቴጂካዊ ምሰሶዎች አንዱ መሆን መቻሉንም አብራርተዋል።

ይህ ዓይነቱ ስር ነቀል ለውጥ ሊመዘገብ የቻለው መንግሥት በወሰዳቸው ቁርጠኛ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የገበያ ሥርዓቱን በማስተካከል እና እሴትን መጨመር በሚያስችሉ መጠነ-ሰፊ ኢንቨስትመንቶች በመታገዙ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አስገንዝበዋል።

ሪፎርሙን ተከትሎ ማዕድንና ነዳጅን እንደ እምቅ አቅም ብቻ ከማውራት ባለፈ፣ተጨባጭ ውጤት ወደሚያስመዘግብ ስትራቴጂካዊ አቅም እንዲሸጋገር መደረጉን አመልክተዋል።

መንግሥት በዘርፉ የነበሩ የአሠራር እንቅፋቶችን ለማስወገድ ህግጋትን ያሻሻለ ሲሆን፣ ግልጽነትን ለማረጋገጥም የዲጂታል አሠራሮችን ማስተዋወቁን አመልክተዋል።

አሁን የተዘረጋው ሥርዓት ዘርፉን ከቁጥጥር ባለፈ ከኢንቨስተሮች ጋር ጠንካራ አጋርነት በመፍጠር ለአስተማማኝና ለረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት ምቹ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ዘርፉ ከፍተኛ የወጪ ንግድ ኤክስፖርት ገቢን ለሀገር እያስገኘ ሲሆን፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ጥገኝነት በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ለከሰል ድንጋይ ማስገቢያ በየዓመቱ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታወጣ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ አምራቾችንና የግል ባለሀብቶችን በማበረታታት የሀገሪቱን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን መቻሉን ገልጸዋል።

የሲሚንቶ ምርትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ የሀገሪቱ ዓመታዊ የሲሚንቶ ምርት ከ8 ሚሊዮን ቶን ወደ 14 ሚሊዮን ቶን በማደጉ ገበያውን ማረጋጋት መቻሉን አስታውቀዋል።

በወርቅ፣በስትራቴጂካዊና ወሳኝ ማዕድናት፣በነዳጅ እንዲሁም በማዳበሪያ ምርት ላይ እየተስፋፉ የመጡት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች የለውጡ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በማዕድኑ ዘርፍ እየታዩ ያሉ ስኬቶች የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣የስትራቴጂካዊ ርዕይ እና የተቀናጀ የአፈጻጸም ድምር ውጤት መሆናቸውን ኢንጂነር ሐና ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያሸጋግር በትኩረት እየተሠራበት መሆኑ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም