ቀጥታ፡

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ አዲስ የዓለም ዋንጫ ክብረ ወሰን ባስመዘገበበት ጨዋታ ፖርቹጋል በሰፊ የግብ ልዩነት አሸነፈች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የምድብ 11 መርሐ ግብር ፖርቹጋል ኡዝቤኪስታንን 5 ለ 0 አሸንፋለች።

ማምሻውን በሂውስተን ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ኑኖ ሜንዴዝ፣ ራፋኤል ሊያዎ እና የኡዝቤኪስታኑ ግብ ጠባቂ አብዱቮሂድ ኔማቶቭ በራሱ ላይ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

የ41 ዓመቱ የፖርቹጋል አምበል ክርስቲያኖ ሮናልዶ በስድስት የዓለም ዋንጫዎች ግብ ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች በመሆን አዲስ ታሪክ ጽፏል።

በዓለም ዋንጫው ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 10 በማድረስ ለፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ብዙ የአለም ዋንጫ ጎል ያስቆጠረው ተጫዋች ሆኗል።

ከዚህ ቀደም ኡሴቢዮ ለፖርቹጋል ዘጠኝ ግቦችን በማስቆጠር ክብረ ወሰኑን ይዞ ነበር።




ሮናልዶ ከካሜሮኑ ሮጀር ሚላ (42 ዓመት) በመቀጠል በዓለም ዋንጫው ግብ ያስቆጠረ ሁለተኛው አንጋፋ ተጫዋች ሆኗል።

በተጨማሪም ሮናልዶ ለሀገሩ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት 145 ያደረሰ ሲሆን በእግር ኳስ ህይወቱ ከመረብ ላይ ያሳረፋቸውን ግቦች ብዛት 975 አድርሷል።

በጨዋታው የፖርቹጋል የበላይነት በጉልህ ታይቷል።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ድሏን ያስመዘገበችው ፖርቹጋል በአራት ነጥብ የምድብ 11 መሪ ሆናለች። ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድሏንም አስፍታለች።

በውድድሩ ሁለተኛ ሽንፈቷን ያስተናገደችው ኡዝቤኪስታን ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድሏ ጠባብ ሆኗል።




ኡዝቤኪስታን ለዓለም ዋንጫው ስትሳተፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በዚሁ ምድብ ኮሎምቢያ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ በጓድላሃራ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በመጀመሪያ ጨዋታዋ ኮሎምቢያ ያሸነፈች ሲሆን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ደግሞ አቻ ተለያይታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም