አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የከተሞች የፋይናንስ ድጋፍ ጥምረትን ተቀላቀለች - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የከተሞች የፋይናንስ ድጋፍ ጥምረትን ተቀላቀለች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ጥራትን ለማሻሻል እና የማህበረሰብ ጤናን ለመጠበቅ ለሚከናወኑ ስራዎች የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግበትን “የብሪዝ ሲቲስ ኔትወርክ” በአባልነት ተቀላቅላለች።
የለንደን የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ሳምንት መካሄዱን ቀጥሏል።
በዛሬው ስብስባ ላይ አዲስ አበባ የ”ብሪዝ ሲቲስ” ከተሞች አባል መሆኗ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ፕሮግራሙ በብሉምበርግ ግብረ ሠናይ የድርጅት፣ “በክሊን ኤር ፈንድ” እና “በሲ40 ሲቲስ” አማካኝነት ድጋፍ ይደረግለታል።
ብሉምበርግ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ የአየር ጥራትን ለማሻሻል 45 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ በዓለም ላይ ከተመረጡ ከተሞች ጋር በትብብር የሚሰራበትን ፕሮግራም ይፋ አድርጓል።
አላማውም የመዲናዋን የአየር ጥራት ለማሻሻልና ከአየር ጥራት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የጤና ጉዳት ለመቀነስ ያለመ ነው።
ይኽም አዲስ አበባን ጨምሮ በ16 ዓለም አቀፍ ከተሞች የሚተገበር ይሆናል።
የፕሮግራሙ ይፋ መሆን ተከትሎ፥ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት አዲስ አበባ የብሪዝ ሲቲ አባል መሆኗ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ እያሳየ ያለውን ሁለንተናዊ የላቀ የከተማ ትራንስፎርሜሽን፤ ፅዱ፣ ውብ፣ አረንጓዴ እና ለመኖር ምቹ ከባቢን ከመፍጠር ስራ ጎን-ለጎን የአረንጓዴ አሻራ፣ የብስክሌት መንገድ እና የአየር ጥራት መቆጣጠርያ መሳሪያዎችን የበለጠ አስፋፍቶ እና አጠናክሮ ለመስራት ያግዛል ብለዋል።
በቀድሞው የኒውዮርክ ከንቲባ ማይክል ብሉምበርግ በሚመሩት የግብረ ሰናይ ድርጅት እየተደረገ ያለው እገዛም የተጀመረውን ስራ አጠናክሮ ለመስራት እንደሚያስችል አመልክተዋል።
በተጨማሪም ፕሮግራሙ አዲስ አበባ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) ስታዘጋጅ በአየር ጥራት ቁጥጥር እና የአየር ጥራትን ማሻሻል የሚያስችሉ ተሞክሮዎችን ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ብሎም ለአለም አቀፍ ከተሞች ተሞክሮ ለማሳየት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ልዩ መልዕክተኛ እና የብሉምበርግ ግብረ ሰናይ ድርጅት ዋና መስራች ማይክል ብሉምበርግ በበኩላቸው፣ በብሪዝ ሲቲስ አማካኝነት የከተማ ከንቲባዎች እንዲሁም መሪዎች የአየር ጥራትን ከማሻሻል አንጻር ግንባር ቀደም ሆነው መስራት መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
እያንዳንዱ ከተማ ወደፊት የአየር ጥራትን ከማሻሻል አንጻር የሚወስደው እርምጃ ሕይወትን ለማዳን፣ የሕዝብ ጤናን ለማሻሻል እና የብክለትን ልቀትን ለመቀነስ እንደሚረዳ ጠቅሰው፤ ይህም ከተሞችን ለመኖርና ለመሥራት የተሻሉ ቦታዎች እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።
ይህ አዲስ ኢንቨስትመንት ወይም ድጋፍ ከንቲባዎች እያደረጉ ባለው ስራ ተጨማሪ እገዛ ያደርጋል፤ ከነዚህ ስራዎች የሚገኙ ተሞክሮዎችንም ወደ ተጨማሪ ከተሞች ለማድረስ ያግዛል ብለዋል።
ዛሬ ከተቀላቀሉት አዲስ አበባ እና ማድሪድ ከተሞች በተጨማሪ፥ አክራ፣ ባንኮክ፣ ቦጎታ፣ ብራስልስ፣ ጃካርታ፣ ጆሃንስበርግ፣ ለንደን፣ ሜክሲኮ ሲቲ፣ ሚላን፣ ናይሮቢ፣ ፓሪስ፣ ሪዮ ዴ ጄኔሮ፣ ሶፊያ፣ እና ዋርሶ የብሪስ ሲቲስ ፕሮግራም ተጠቃሚ ከተሞች ናቸው።
ይህም ብክለትን ለመቀነስ እና የህዝብ ጤናን ለማሻሻል የሚሰሩ ከንቲባዎችን ትብብር ለማጠናከር የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተመላክቷል።
ሰኔ 13 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው የለንደን የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ሳምንት እስከ ሰኔ 21 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።