መንግሥት በመደመር እሳቤ ዘመን ተሻጋሪና ሜጋ መሠረተ ልማቶችን እውን አድርጓል-ብሩክ ታዬ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት በመደመር እሳቤ ዘመን ተሻጋሪና ሜጋ መሠረተ ልማቶችን እውን አድርጓል-ብሩክ ታዬ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦የለውጡ መንግሥት በመደመር እሳቤ ውጤታማ የፋይናንስ ሥርዓትን በመከተል ለትውልድ የሚሻገሩ ሜጋ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን እውን ማድረጉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት "ከለውጥ ወደ ዘላቂ ሽግግር" በሚል መሪ ሀሳብ "ኢትዮጵያ ታከናውናለች" ጉባኤ በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፥ የኢትዮጵያ የመሠረተ-ልማት ጉዞ ለዘመናት ከዘለቀው ሀገራዊ ትልም ተነሥቶ፣ አሁን ላይ በትጉህና ግልጽ መርሆዎች እንዲሁም በተቀናጀ አፈጻጸም ወደሚመራ የለውጥ ዘመን መሸጋገሩን ገልጸዋል።
ለዚህ ስኬት ደግሞ የለውጡ መንግሥት ሀገራዊ ተስፋን ከተቋማዊ አቅም ጋር ወደሚያጣጥም፣ ይበልጥ አመቺ፣ ቅደም ተከተላዊ እና የፋይናንስ ሥርዓትን ወደ ተከተለ አካሄድ ቁርጠኛ ሽግግር በማድረጉ የተመዘገበ ነው ብለዋል።
የእያንዳንዱ ውጤት መሠረትም የለውጡ መንግስት የተከተለው የመደመር እሳቤ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ የመደመር እሳቤ አካሄድም መሠረተ ልማትን ወደ ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ እሴት እና ለትውልድ ተሻጋሪ ሀብት እንዲቀየር እያደረገው እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የታዳሽ ሃይል፣ የዲጂታል ማስፋፊያ፣ የትራንስፖርት፣ የኮንስትራክሽን እና የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ሀገሪቱ የምታደርገውን የለውጥና የብልጽግና ጉዞ እየመሩት እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ፈጣን እድገቷን ለማስቀጠል እየተጋች እንደምትገኝ በማብራሪያቸው ላይ አመላክተዋል።
በዚህም በርካታ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግስት መሠረተ-ልማትን በተመለከተ ውጤታማ የሆኑ አሠራሮችን በቀጣይነት በመተግበሩ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።