ባለፉት ስምንት ዓመታት በውጭ ዕዳ ጫና ቅነሳ፣ በውጭ ምንዛሬ አስተዳደርና በዋጋ ንረት ቅነሳ ትርጉም ያለው ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስምንት ዓመታት በውጭ ዕዳ ጫና ቅነሳ፣ በውጭ ምንዛሬ አስተዳደርና በዋጋ ንረት ቅነሳ ትርጉም ያለው ውጤት ተመዝግቧል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በውጭ ዕዳ ጫና ቅነሳ፣ በውጭ ምንዛሬ አስተዳደርና በዋጋ ንረት ቅነሳ ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እየብ ተካልኝ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት “ከለውጥ ወደ ዘላቂ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ የ“ኢትዮጵያ ታከናውናለች” ጉባኤ በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እየብ ተካልኝ (ዶ/ር) ባለፉት ስምንት ዓመታት በሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተወሰዱ እርምጃዎች የተገኙ ውጤቶች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ በግብርና፣ ማዕድን፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና ዲጂታል መስኮች ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገብ ማስቻሉን አንስተዋል።
ከለውጡ በፊት የውጭ ዕዳ ጫና ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰው፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም ከመደበኛው የዶላር ምንዛሬ የጥቁር ገበያው ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ መብለጡ ትልቅ ችግር እንደነበር አንስተዋል።
ሪፎርሙ የዕዳን ጫናን ለመቀነስ ከማስቻሉም ባሻገር የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግሮች እንዲቀረፉ ማድረጉን አመልክተዋል።
የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሬን ገበያ መር በማድረግ፣ የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲን በማዘመን ትርጉም ያለው ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
በዚህም የፋይናንስ ዘርፉን የሚያጠናክሩ ተግባራት ተከናውነዋል ያሉት ገዥው ለዘላቂና አካታች ዕድገት ጠንካራ መሠረት ተጥሏል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበቱ እስከ 34 በመቶ የደረሰበት ጊዜ እንደነበር ያስታወሱት እዮብ (ዶ/ር) በተወሰደው የማሻሻያ እርምጃ የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ መቻሉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ገቢ እያደገ መምጣቱን ገልጸው ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ተወዳዳሪነት እየጨመረ ነው ብለዋል።
ይህም የተወሰደው የማሻሻያ ውጤት መሆኑንም በማብራሪያቸው አመልክተዋል።