ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ነጻና ተምሳሌታዊ ነው - አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ነጻና ተምሳሌታዊ ነው - አምባሳደሮች
አዲስ አበባ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተምሳሌታዊ ምርጫ ነው ሲሉ የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች ገለጹ።
በዛሬው ዕለት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ካቀረቡት የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች መካከል ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት፣ ኢትዮጵያ ያካሄደችው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ገልጸዋል።
የናይጄሪያ አምባሳደር ናሲር አሚኖ፤ በኢትዮጵያ የተካሄደው ነፃ፣ ፍትሐዊና ተአማኒነት ያለው ምርጫ በመሆኑ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በምርጫ ሂደት ላይ ቴክኖሎጂ መጠቀም መቻሉን ያደነቁት አምባሳደሩ፤ የታየው ከፍተኛ የመራጮች ቁጥር ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ትልቅ ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።
የጋና አምባሳደር ማክአሪዮስ አካንቤአናብ አካንቦንግ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ምርጫን በነፃና ፍትሐዊ መንገድ በማካሄድ ሰላም ማምጣት እንደሚቻል በተግባር ማሳየቷን ገልጸዋል።
ይህ ለአብዛኞቹ ትልቅ ፈተናና ተግዳሮት በሆነበት ወቅት ኢትዮጵያ በሰለጠነ መንገድ መልስ የሰጠችበት እንደሆነ አምባሳደሩ አብራርተዋል።
የስሪላንካ አምባሳደር ኒርማላ ኢንዱማቲ ዲያስ ፓራናቪታና፣ ምርጫው እጅግ ስኬታማና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መከናወኑን አንስተዋል።
አምባሳደሯ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመምረጥ መብቱን በአግባቡ መጠቀም በመቻሉም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የፖርቹጋል አምባሳደር ጆርጅ ፔሬራ ዶ ናሲሜንቶ፣ በምርጫው ወቅት የታየው የሕዝቡ ከፍተኛ ተሳትፎና የዴሞክራሲ አካሄድ ዋናውና ትልቁ ስኬት መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ ስኬት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕድገትና ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት እንደሚያመጣ እምነታቸውን ገልጸዋል።