ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሁሉም ዘርፍ ለትውልድ የሚሻገር የላቀ ዕድገት እያስመዘገበ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሁሉም ዘርፍ ለትውልድ የሚሻገር የላቀ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት “ከለውጥ ወደ ዘላቂ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ የ“ኢትዮጵያ ታከናውናለች” ጉባኤ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለዘመናት ጠብቃ የቆየች የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ሀገር ናት።

በ21ኛው ክፍለ ዘመንም ሕዝቦቿን በማስተባበር ያለማንም ድጋፍ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ የገነባች የልማት ተምሳሌት መሆኗን አውስተዋል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ዕድገትን ከማፋጠን ባሻገር ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስተላለፍ በተከናወኑ ተግባራት ዘርፈ ብዙ ስኬት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት በአዲስ የስኬት ምዕራፍ እየተጓዘ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለአብነትም ከ30 በመቶ በላይ ደርሶ የነበረውን የዋጋ ንረት ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ መቻሉን አስረድተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም የውጭ ንግድ ተወዳዳሪነት አቅምን በማሳደግ ጭምር ኢትዮጵያ የ10 ነጥብ 2 በመቶ የአፍሪካን ፈጣን ዕድገት እንደምታስመዘግብ አስረድተዋል።

እነዚህ ውጤቶች በአጋጣሚ ያልተገኙና የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በጥንቃቄ ተግባራዊ የተደረገው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ ውጤት መሆናቸውን ነው ያብራሩት።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራም በመደመር መርህ ዕድገትን የሚያሳልጡ የአሠራር ሥርዓቶች ተግባራዊ መሆናቸውን አብራርተዋል።

መደመር የአብሮነት እውነተኛ ትርጉም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መደመር ዕድገት የሚጠናከረው የተለያዩ ጥረቶች እርስ በርስ ሲደጋገፉ መሆኑን ያምናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የብዝሃ ኢኮኖሚ ዕድገት እመርታን ለማስቀጠል በከፍተኛ ትጋት እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ የሚያሳልጥ ትብብርና አጋርነት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ የማንሠራራት ጉዞ በማጽናት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማስቀጠል የተሻለች ሀገርን ለትውልድ የማሻገር ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም