ቀጥታ፡

ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ከተረጂነት ለመላቀቅ የተያዘውን ዕቅድ የሚያሳኩ ናቸው

አሶሳ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ከተረጂነት ለመላቀቅ የተያዘውን ዕቅድ የሚያሳኩ ናቸው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተረጂነት ቅነሳና በምግብ ሉዓላዊነት ዙሪያ በተዘጋጀ የ5 ወራት ዕቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ወቅትም እንደተናገሩት፤ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ከተረጂነት ለመላቀቅ የተያዘውን ዕቅድ የሚያሳኩ ናቸው።

በክልሉ በቅርብ ዓመታት የተጀመረው ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ትግበራ አበረታች ውጤት የታየበትና የስራ ባህልን የቀየረ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በቂ ምርትን በመያዝ አደጋን የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሐመድ አብዱላዚዝ በበኩላቸው፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት በግብርናው ዘርፍ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን በማምረት ለአደጋ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም