ቀጥታ፡

በክልሉ ምርታማነትን በማሳደግ ስርዓተ ምግብን በቤተሰብ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው 

ባህር ዳር ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦  በአማራ ክልል ምርታማነትን በማሳደግ ስርዓተ ምግብን በቤተሰብ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ  መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው በምግብ ማበልፀግ ዙሪያና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚመክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ አካሄዷል።


 

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ መልካሙ ጌትነት በመድረኩ እንዳሉት፤ በክልሉ በቂና የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽ ለማድረግ ባለድርሻ ተቋማትን ያሳተፈ ስራ እየተሰራ ይገኛል።

በዚህም ምርታማነትን በማሳደግ ስርዓተ ምግብን በቤተሰብ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ማህበረሰቡ ከልማዳዊ አመጋገብ በመውጣት ሁሉንም የምግብ ዓይነቶች አሰባጥሮ እንዲመገብ ጠንካራ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በፋብሪካዎች የስንዴ ዱቄትና ዘይትን አስፈላጊ በሆኑ ንጥረ ነገሮች አበልጽጎ በማምረት ለምግብነት የማዋል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እንዲሁም ማህበረሰቡ ባለው ትንሽ መሬት ሁሉ አትክልት፣  ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬና ሌሎች ሰብሎችን በአነስተኛ መሬት አልምቶ እንዲጠቀም ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም በትምህርት ቤቶች የተጀመረው የምገባ መርሃ ግብር ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው በአካልና በአዕምሮ እንዲዳብሩ ስለሚያደርግ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በመሆኑም ስርዓተ ምግብ በክልሉ ችግር እንዳይሆን በቅንጅት እየተሰራ ያለው ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


 

በኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የባህር ዳር ቅርንጫፍ የምግብ ቁጥጥር ባለሙያ አቶ መለሰ እንግዳየሁ በበኩላቸው፤ በምግብና መድኃኒት ውጤቶች ላይ ቁጥጥር በማድረግ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ምግብና መድኃኒቶች ተገቢውን የጥራት ደረጃ ጠብቀው ለአገልግሎት እንዲውሉ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በህገ ወጥ መንገድ ለገበያ የሚቀርቡት ላይ ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበርም አሳስበዋል።

በመድረኩም ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት ላይ የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት መወያየታቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም