ለገጠሩ ማህበረሰብ ታዳሽ ኃይልን ተደራሽ በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነቱን የማጎልበት ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለገጠሩ ማህበረሰብ ታዳሽ ኃይልን ተደራሽ በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነቱን የማጎልበት ተግባር እየተከናወነ ነው
አዳማ ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ ለገጠሩ ማህበረሰብ ታዳሽ ኃይልን ተደራሽ በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነቱን የማጎልበት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) ጋር በመተባበር በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የሶላር ሚኒ ግሪድ ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና በአዳማ ከተማ እየሰጠ ይገኛል።
በወቅቱም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚኒ ግሪድ ፕሮግራም ዩ.ኤን.ዲ.ፒ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ይመስላል ተፈራ እንደገለፁት፤ ሚኒስቴሩ በ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ከዋና የኃይል መስመር ውጪ ያሉ የገጠር መንደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሶላር ሚኒ ግሪድ የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ ቀርጿል።
በፕሮጀክቱም በተለያዩ ክልሎች ሶስት የሶላር ሚኒ ግሪዶችን ለመትከል የሚያስችል የዲዛይን ዶክመንት መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
ከዋና መስመር ውጪ የሆኑ አካባቢዎችን በኃይል አቅርቦት ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀየሱት ሶስቱ የሶላር ሚኒ ግሪዶች 624 ኪሎ ዋት ኃይል በማመንጨት 31 ሺህ ነዋሪዎችን የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላሉ ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋፋት፣ ፈጠራንና የግል ዘርፉን ለማበረታታት እንዲሁም ዘላቂ የኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኢኮኖሚ እድገትን ለማሳለጥ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱን ወደ ትግበራ ለማስገባትም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠናው ዛሬ መጀመሩን ተናግረዋል።
በሚኒስቴሩ የገጠር ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማስተዋወቅ ዴስክ ሃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሌ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሃይድሮ፣ የፀሐይ፣ የንፋስ፣ የሶላር እና የባዮ ማስ ኢነርጂ ሰፊ ሀብት እንዳላት አስታውቀዋል።
ይህንን የተፈጥሮ ጸጋ ታሳቢ በማድረግ ፍትሃዊ እና ዘመናዊ የኃይል አቅርቦትን ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህ ረገድ አነስተኛ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ግሪዶችን ከዋና መስመር የኃይል አቅርቦት ለራቁ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ መሰራቱን አንስተዋል።
ከሚኒ ግሪድ ልማት በተጨማሪም በገጠር በቤተሰብ ደረጃ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።