በክልሉ መንግስታዊ አሰራርን ለማቀላጠፍ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነት እየተስፋፋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ መንግስታዊ አሰራርን ለማቀላጠፍ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነት እየተስፋፋ ነው
ቁሊቶ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተደራሽነት በማስፋት ለመንግስታዊ አሰራር ጥራትና ቅልጥፍና ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የሀላባ ቁሊቶን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ዛሬ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተደራሽነት በማስፋት ለማህበረሰቡ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተበታተኑ አገልግሎቶችን በማሰባሰብ ማህበረሰቡ አገልግሎት በአንድ ቦታ በቅርበት እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም ማህበረሰቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ የሚገጥመውን እንግልት ከማስቀረት ባለፈ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻሉን እንዳሻው (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በክልሉ አገልግሎትን በማስፋት ለማህበረሰቡ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በክልሉ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሰል የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ የማስቀጠል ሥራም በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አያይዘው ገልጸዋል።
የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን ሁሴን በበኩላቸው፤ መንግስት ለማህበረሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ የማህበረሰቡን እንግልት የሚያስቀር መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዛሬ የተመረቀው የሃላባ ቁሊቶ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሦስት የፌዴራል ተቋማት እና በአራት የክልል ተቋማት 42 አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ለመስጠት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
ማዕከሉ የመንግስት አገልግሎትን ለማግኘት ማህበረሰቡ ከቦታ ቦታ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚያስቀር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ገመዳ መሀመድ ናቸው፡፡
ማዕከሉ ለከተማዋ ነዋሪዎች ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።
በአገልግሎቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።