በአስተዳደሩ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ይከናወናሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአስተዳደሩ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ይከናወናሉ
ሰቆጣ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በክረምት ወራት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት እንደሚከናወኑ ተገለጸ።
በአስተዳደሩ የሰቆጣ ከተማ ወጣቶችም በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ የ2018 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የብሔረሰብ አስተዳደሩ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ትበርህ ታደሰ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በዘንድሮ ክረምት 197 ሺህ 250 ዜጎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሳተፍ ታቅዷል።
በተለያየ ዘርፍ በሚሰጡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችም 584 ሺህ 860 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።
የተጠናከረና ውጤታማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማከነውንም የንቅናቄ መድረኮች እስከ ቀበሌ ድረስ እንደሚካሄዱ ወይዘሮ ትበርህ ተናግረዋል።
"የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የትብብርና የመተሳሰብ እሴትን ያጠናክራል" ያሉት ደግሞ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በምክትል አስተዳዳሪ ማዕረግ የመንገድ፣ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ መምሪያ ሃላፊ አቶ ፀጋው እሸቴ ናቸው።
አገልግሎቱ የማህበረሰብ እውቀት፣ ክህሎትና አቅምን በማቀናጀት ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች የሚከናወኑበት በመሆኑ ሁሉም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች በበኩላቸው በዘንድሮው ክረምት በሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ላይ በየደረጃው የሚገኙ ወጣቶችን የሚያስተባብሩና በጎ ፈቃደኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።