ቀጥታ፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የአየርላንድ አምባሳደር ኦሊቪያ ሌስሊን አሰናበቱ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የአየርላንድ አምባሳደር ኦሊቪያ ሌስሊን አሰናብተዋል።

አምባሳደር ኦሊቪያ ሌስሊ በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ያሳለፉት የዲፕሎማሲ ዘመን እጅግ ስኬታማ፣ አስደናቂና በበጎ ተሞክሮዎች የተሞላ ነው።

በቆይታቸው በመላው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመዘዋወር ዕድል ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በየክልሎቹ የተደረገላቸው አቀባበል ለሥራቸው ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረ እንደነበር ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ሥራዎችን መስራታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያና የአየርላንድ ግንኙነት ይበልጥ እያደገ፣ ከጥንካሬ ወደ ጥንካሬ ሲሸጋገር ማየት የዘወትር ምኞታቸው መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ዲፕሎማሲያዊ ሚና መወጣታቸው በግልም ሆነ በሙያዊ ሕይወታቸው ትልቅ ትርጉም እንዳለው አረጋግጠዋል።

በቀጣይም ሁለቱ ሀገራት በሰው ሀብት ልማት ዘርፎች ላይ በትብብር መስራት እንደሚገባቸው አመልክተው፤ ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነትን ለማስፋት የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን ማጠናከር ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድና የኢኮኖሚ ግንኙነት ከፍተኛ እምቅ አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ዕድል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በጋራ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አምባሳደር ኦሊቪያ ሌስሊ በቆይታቸው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም