ቀጥታ፡

ኢጋድ በ7ኛው አጠቃላይ ምርጫ ስኬታማነት ለኢትዮጵያዊያን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፈ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ) ፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) በ7ኛው አጠቃላይ ምርጫ ስኬታማነት ለኢትዮጵያዊያን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አብዛኛውን የምክር ቤት ወንበሮች ብልጽግና ፓርቲ ማሸነፉን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ይሄንን ተከትሎ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን ባወጣው መግለጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው 7ኛው አጠቃላይ ምርጫ ስኬታማ አካሄድ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

በምርጫው አብላጫ ድምፅ ያገኘውን ብልጽግና ፓርቲን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ን እንኳን ደስ ያላችሁ ብሏል።

ኢጋድ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደቱን በመምራት ረገድ ላሳየው ሙያዊ ብቃትና ቁርጠኝነት ምስጋና ያቀረበ ሲሆን ምርጫው በሰላማዊና በሥርዓት እንዲጠናቀቅ ባደረጉት ተሳትፎም የኢትዮጵያን ሕዝብ አድንቋል።

የምርጫው በስኬት መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ያላትን ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ ነው ብሏል በመልዕክቱ።

ሀገሪቱ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ አካታች ውይይትን ለማሳደግ እንዲሁም ሰላምን፣ መረጋጋትንና ዘላቂ ልማትን ለማስፈን ለምታደርገው ቀጣይ ጥረት ያለውን ድጋፍም ገልጿል።

ኢጋድ በቀጣናው ትብብርን፣ ውህደትን፣ ሰላምን፣ መረጋጋትንና ዘላቂ ልማትን ለማስቀጠል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋግጣል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም