ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አሸናፊነት ያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አሸናፊነት ያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ተዓማኒ ሆኖ መጠናቀቁ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አሸናፊነት ያረጋገጠ መሆኑን የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት (ኢዴኅ) ገለጸ።
የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት (ኢዴኅ) ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደገለጸው፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ተዓማኒ ሆኖ መጠናቀቁ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አሸናፊነት ያረጋገጠ ነው።
አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ የተጣለበትን ታላቅ ሕዝባዊ አደራ በመቀበል፣ የመረጠውንም ሆነ ያልመረጠውን ሕዝብ በእኩል በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል ይጠበቅበታል ብሏል።
በምርጫውን ላሸነፈው ብልፅግና ፓርቲም የእንኳን ደስያለህ መልዕክት በማቅረብ መልካም የሥራ ዘመን ተመኝቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሂደቱን በገለልተኝነት፣ በብቃትና በትዕግስት በመምራት የሕዝብ አገልጋይነቱን በተግባር ማሳየቱን ገልጿል።
ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ሌት ተቀን በመሥራት ኃላፊነቱን በብቃት መወጣቱንም ጠቁሟል።
አገሪቷ ካጋጠሟት በርካታ ተግዳሮቶች አኳያ እጅግ ውስብስብ የሆኑ አገራዊ ሂደቶችን በከፍተኛ ሙያዊ ብቃት፣ ገለልተኝነት እና ግልጽነት በመምራት ረገድ የምርጫ ቦርድ ሚና የሚደነቅ መሆኑን አመልክቷል።
ቦርዱ ያጋጠሙትን ችግሮች በግልጽ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ፣ የሕዝብን ድምጽ ለመጠበቅና ሰላማዊ የዲሞክራሲ ምህዳር ለመፍጠር ያደረገው ጥረት ታሪክ የማይዘነጋው አኩሪ ተግባር በመሆኑ ከፍተኛ አድናቆቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ የብልፅግና ፓርቲ በሕዝብ ተወካዮችና በክልል ምክር ቤቶች አብላጫ መቀመጫ ማግኘቱ መገለጹ ይታወሳል።