ከተማዋ ያሏትን ፀጋዎች በአግባቡ በማልማት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ከተማዋ ያሏትን ፀጋዎች በአግባቡ በማልማት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ
አርባ ምንጭ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ አርባምንጭ ከተማ ያሏትን ፀጋዎች በአግባቡ በማልማት ማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።
መንግስት የከተሞችን ገጽታ በመለወጥ ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በዚህም በሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች በስፋት እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር፣ የወንዝና የሀይቅ ዳርቻ የልማት ስራዎች ገፅታን ከመቀየር ያለፈ ግብን ይዘው እየተከናወኑ ነው።
ይህም ከተሞቹን ለኑሮ፣ ለስራ፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ በማድረግ ፈጣን ዕድገት እንዲያስመዘግቡ እያገዘ ሲሆን የአርባ ምንጭ ከተማም በልማት ስራዎቹ በፈጣን ዕድገት ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች አንዷ እየሆነች ነው።
የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ከተማዋ ያሏትን ፀጋዎች በአግባቡ በማልማት ማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ።
የለውጡ መንግስት ከተሞችን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በዘረጋው ትልም የከተማዋ ፀጋዎች ተገልጠው ወደ ሀብት እየተቀየሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የእግረኞች፣ የብስክሌት፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የህዝብ መዝናኛ፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ያካተተ 20 ኪሎ ሜትር የተቀናጀ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ከእነዚህም በተለየ ስያሜ እየተገነቡ ያሉ የደረጃ መንገዶችን ጨምሮ የኩልፎ ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች የከተማዋን ፈጣን ዕድገት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
በከተማው በመንግስትና በህዝቡ ተሳትፎ የተገነቡ የህክምና ተቋማትና ደረጃውን የጠበቀ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መኖሩን ጠቅሰው የከተማዋን ዕድገት ለማፋጠን እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ እየተከናወኑ የሚገኙ አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ዕድገት እያፋጠኑ መሆኑን መስክረዋል።
አቶ ሙሴ ጉማራ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ እንደገለፁት፤ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉት የኮሪደር፣ የወንዝ ዳርቻና የስታዲየም ግንባታዎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በከተማዋ ፈጣን ዕድገት እንዲመጣ እያደረጉ ነው ብለዋል።
የመንገድ እና የመብራት መሠረተ ልማቶች እንዲሁም የቤቶች፣ የጤና እና የትምህርት ተቋማት ዘመኑን በሚመጥን መልኩ በመገንባታቸው የከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እየተረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።