ቀጥታ፡

በካፋ ዞን የሚገኙ ሀብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል

ቦንጋ ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ በካፋ ዞን የሚገኙ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የካፋ ዘመን መለወጫ በዓል (ማሽቃሮ) በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተጠና ጥናት የመጀመሪያ ዙር የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሄዷል።



በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፤ የካፋ ሕዝብ የበርካታ ባሕላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች ባለቤት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከነዚህም የዘመን መለወጫ በዓል "ማሽቃሮ" አንዱ መሆኑን ጠቁመው በተገቢው ጥናት ተደግፎና ለምቶ በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ዞኑ በርካታ የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሃብት መገኛ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የካፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ታሪኳ ታከለ ናቸው።


 

የካፋ ዘመን መለወጫ በዓል "ማሽቃሮ"ን በማስተዋወቅ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ በየደረጃው ሲቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎችን በመቀበል የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጥናት ሲያካሄድ ቆይቶ ለውይይት ማቅረቡን ገልፀዋል።

የጥናት ፅሁፉን ለመድረኩ ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የባህል እሴቶች ጥናትና ልማት ባለሙያው አቶ ማህተቤ ጥላሁን፤ ሚኒስቴሩ የሕዝቦችን ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች በማጥናት፣ በመሰነድና በማስተዋወቅ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ በሰፊው እየሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

በዚህም የካፋ ዘመን መለወጫ በዓል "ማሽቃሮ" የባህል መዳረሻ ሆኖ እንዲተዋወቅና በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ሲደረግ የነበረውን ጥናት በማጠናቀቅ የመጀመሪያ ዙር ውይይት ተደርጎ ለቀጣይ ስራ የሚጠቅም ግብዓት መገኘቱን ተናግረዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል  የካፋ ባህል ልማት አማካሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ሀይሌ ፤ ማሽቃሮ በካፋ ህዝብ ዘንድ ለበርካታ ዘመናት ያለልዩነት የሚከበር አንድነትን፣ ሰላምንና ፍቅርን የሚያጠናክር በዓል መሆኑን ገልፀዋል።


 

በዓሉ ካለው ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አንፃር ከአካባቢው አልፎ በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ፣ ይበልጥ እንዲለማና የባህል መዳረሻ ሆኖ በቀጣይነት ለትውልድ እንዲተላለፍ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም