ቀጥታ፡

የተማሪዎችን የፈጠራ ተነሳሽነትና አቅም በሞራልና በቁሳቁስ መደገፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ሊሆን ይገባል

ባህር ዳር፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦የተማሪዎችን የፈጠራ ተነሳሽነትና አቅም በሞራልና በቁሳቁስ መደገፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ክልላዊ የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይና የጥናትና ምርምር ሲምፖዚየም በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።

በወቅቱም ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የተማሪዎችን የፈጠራ ተነሳሽነትና አቅም በሞራልና በቁሳቁስ መደገፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።


 

ወጣት ተመራማሪዎች በአካባቢያቸው የሚገኙ ተግዳሮቶችን አልፎ ለመሄድ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎች ላይ በማተኮር መስራት አለባቸው ብለዋል።

በትምህርት ቤቶች አሁን ላይ የሚታዩ የፈጠራ ስራዎች መነሳሳትን በማድነቅ የተማሪዎች የመፍጠር አቅም ማሳደግ ላይ የተጠናከረ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ተመራማሪዎች የሚያጋጥሟቸውን የቁሳቁስና የፋይናንስ ችግር ለመፍታት መንግስት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ በፈጠራው መስክ ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ ኢትዮጵያውያን ምሁራን እንዳሉ ጠቅሰው፣ ይህንን አቅም በሀገር ውስጥ ለማስፋት የክልሉ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቅነህ በበኩላቸው፣ መድረኩ በትምህርት ዘርፍ የተከናወኑ የፈጠራ ስራዎችንና ጥናቶችን ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።


 

ቢሮው በክልሉ የሚገኙ የሳይንስና የፈጠራ አቅሞችን በቅንጅት ለመምራት፣ ለመደገፍና ለማልማት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በትምህርት ስርዓቱ ተወዳዳሪነትንና ችግር ፈቺ እውቀትን ማስፋፋት የዘርፉ ቁልፍ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፣ የተማሪዎችን የፈጠራ ክህሎት፣ ሃሳብና ተግባር ለማበልጸግ በትኩረት እንደሚሰራም  ተናግረዋል።

በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ከሚፈልግና በትምህርት ጥራት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ከሚያደርግ ማንኛውም አካል ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ቢሮው ዝግጁ መሆኑንም አክለዋል።

በአዊ ብሔረሰብ ዞን የዚገም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው አስማማው ሀብቴ እንደገለጸው፤ በራሱ ሀሳብ፣ አቅምና ጥረት ባለሶስት እግር ባጃጅ በመስራት የፈጠራ ስራውን አቅርቧል።


 

ፈጠራውም በሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ምርቶችን በተግባር መስራት እንደሚቻል ትልቅ ማረጋገጫ መሆኑን ገልጾ እንደዚህ ዓይነት ሲምፖዚየም መዘጋጀቱ ተነሳሽነትን እንደሚፈጥር አመልክቷል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው አውደ ርዕይና ሲምፖዚየሙ ላይም የምርምር ስራዎች የሚቀርቡ ሲሆን በሚያቀርቡት የፈጠራ ስራ ተወዳድረው ለሚያሸንፉ ተማሪዎች ሽልማት እንደተዘጋጀም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም