የኢትዮጵያ የመሠረተ-ልማት ጉዞ በትጉህና ግልጽ መርሆዎች እና በተዋቀረ አፈጻጸም ወደሚመራ የለውጥ ዘመን ተሸጋግሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የመሠረተ-ልማት ጉዞ በትጉህና ግልጽ መርሆዎች እና በተዋቀረ አፈጻጸም ወደሚመራ የለውጥ ዘመን ተሸጋግሯል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የመሠረተ-ልማት ጉዞ ለዘመናት ከዘለቀው ሀገራዊ ትልም ተነሥቶ አሁን ላይ በትጉህና ግልጽ መርሆዎች እንዲሁም በተዋቀረ አፈጻጸም ወደሚመራ የለውጥ ዘመን መሸጋገሩን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ብሩክ ታዬ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት “ከለውጥ ወደ ዘላቂ ሽግግር” በሚል መሪ ቃል የ“ኢትዮጵያ ታከናውናለች” ጉባኤ በመካሄድ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ብሩክ ታዬ በሰጡት ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያ የመሠረተ-ልማት ጉዞ ለዘመናት ከዘለቀው ሀገራዊ ትልም ተነሥቶ አሁን ላይ በትጉህና ግልጽ መርሆዎች እንዲሁም በተዋቀረ አፈጻጸም ወደሚመራ የለውጥ ዘመን ተሸጋግሯል ብለዋል፡፡
ለዚህ ስኬት ደግሞ የለውጡ መንግሥት ሀገራዊ ተስፋን ከተቋማዊ አቅም ጋር ወደሚያጣጥም፣ ይበልጥ አመቺ፣ ቅደም ተከተላዊ እና የፋይናንስ ሥነ-ሥርዓትን ወደ ተከተለ አካሄድ ቁርጠኛ ሽግግር ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህም መሠረተ ልማትን ወደ ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ እሴት እና ለትውልድ ተሻጋሪ ሀብት እንዲቀየር እያደረገው ይገኛል ነው ያሉት።
የንጹሕ ኢነርጂ፣ የዲጂታል ማስፋፊያ፣ የትራንስፖርት፣ የኮንስትራክሽን እና የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ሀገሪቱ የምታደርገውን የለውጥና የብልጽግና ጉዞ እየመሩት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ዕድገቷ ራሱን ችሎ የሚቀጥልና ለውጥ የሚያመጣበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በትጋት እየገነባች ትገኛለች ብለዋል፡፡