ቀጥታ፡

የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ አዲስ ከሚመሰረተው መንግሥት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነን - የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎች

ቦንጋ/ደሴ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች በሀገሪቱ የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ረገድ በብልጽግና ፓርቲ ከሚመሰረተው አዲስ መንግስት ጋር በትብብር ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መሰረት ብልፅግና ፓርቲ አብላጫ የምክር ቤት ወንበር በማግኘት መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምጽ አግኝቷል።

በዚህ ላይ ኢዜአ በቦንጋ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በምርጫው አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብልግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የጀመራቸውና ያስመዘገባቸው የልማት ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

አስተያየታቸውን ከሰጡ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሀብታሙ ነሩ እንዳሉት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝብ ድምጽ ያሸነፈበትና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት መሰረት የጣለበት ነው።

በቀጣይም በምርጫው አብላጫ ድምጽ አግኝቶ መንግስት ከሚመሰርተው የብልጽግና ፓርቲ ጋር በመሆን ለልማት ስራዎች ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።

በጠቅላላ ምርጫው ብልጽግና ፓርቲ የህዝብ ይሁንታ ማግኘቱ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች ያስመዘገባቸውን ድሎች እንዲያስቀጥል ዕድል ይሰጠዋል ብለዋል።

በመሆኑም ፓርቲው በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት እሰራዋለሁ በሚል ለሕዝቡ የገባውን ቃል መተግበር እንዳለበት ገልጸው፤ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌተ ሀገር ለማሸጋገር በሚያደርገው ሂደት የበኩሌን እወጣለሁ ብለዋል

በተለይ በፓርቲው መሪነት ሰላምን ለማስፈንና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ከዳር በማድረስ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የጀመረው ሥራ እንዲጠናከር የድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት አብዮት ካመቶ በበኩሉ ብልፅግና ፓርቲ በሕዝብ ይሁንታ አገኝቶ ዳግም መመረጡ እንደ ሀገር የተተለሙ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማከናወን የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማፋጠን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብሏል።

ፓርቲው የባሕር በርን ጨምሮ ሌሎች ብሔራዊ ጥቅን ለማስከበር እያራመደ ያለው አቋምና እየተከተለ ያለው ዲፕሎማሲያው ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ የሁሉም ዜጎች እገዛ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በልማት፣ በሰላም፣ በመልካም አስተዳደርና በሌሎችም ዘርፎች የያዛቸው ውጥኖች እንዲሳኩና በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለሕዝቡ የገባውን ቃል እንዲፈፅም እንደ አንድ ዜጋ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አቶ አብዮት ገልፀዋል። 

የጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊነት የልማት ሥራዎችን በማጠናከር ሀገርን ለማሻገር የራሱ ድርሻ አለው ያሉት ደግም አቶ አየለ አሰፋ ናቸው።

ይህን ለማሳካትም ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለሕዝቡ የገባውን ቃል ለመተግበር የሚያደርገውን ጥረት እንዲሳካ እንደ ዜጋ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።

በቀጣይ ፓርቲው በኑሮ ውድነት፣ ሰላምን በማፅናትና በመሰረተ ልማት ተደራሽነት ለይ ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም  ገልፀዋል።  

በተመሳሳይ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለስኬት ለማብቃት መትጋት አለበት ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መሰረት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ የምክር ቤት ወንበር በማግኘት አሸናፊ እንደሆነ መገለጹ የሚታወስ ነው።

የምርጫውን ውጤት አስመልክቶ ኢዜአ በደሴ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም በቀጣይ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ሀገራዊ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለስኬት ለማብቃት ሊተጋ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ተስፋዬ ተሾመ ለኢዜአ እንደገለፁት፣ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ድምጻቸውን ከመስጠት ባለፈ ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል።

በጠቅላላ ምርጫው ለሀገር ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አብሮነት ይሰራል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምጻቸውን እንደሰጡ  ገልጸው፣ በቀጣይም ከመንግስት ጋር በመተባባር ለዘላቂ ሰላምና ልማት አበክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል። 

በምርጫው አብላጫ የምክር ቤት ወንበር በማግኘት ያሸነፈው ብልጽግና ፓርቲ ከሚመሰርተው መንግስት ጋር በመተባበር ለሀገር ሰላም፣ ልማትና አብሮነት አበክረው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

ፓርቲው ማሸነፉ የተጀመሩ ሀገራዊና አካባቢያዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ ለመጨረስ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፣  የሚመሰረተው መንግስትም አደዲስ የልማት እቅዶችን ጭምር በማከናወን የህዝብን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንዳለበት ተናግረዋል።

ሌላው የደሴ ከተማ ነዋሪ አቶ ሀብታሙ አድማሱ በበኩላቸው፣ በአብላጫ ድምጽ አሸናፊ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ ከሚመሰረተው መንግስት ዘላቂ ሰላምና ልማት እንጠብቃለን ብለዋል።

ህብረተሰቡ በያለበት በነቂስ ወጥቶ ድምጹን የሰጠው ለነገ ተስፋ በማድረጉ መሆኑን ጠቁመው፣ ፓርቲውም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አከናውነዋለሁ በሚል የገባውን ቃል ፈጥኖ ወደ ተግባር መቀየር እንዳለበት አስረድተዋል።

በተለይ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት፣ ህግ ማስከበር፣ ሙስናና ብልሹ አሰራርን መከላከልና በሌሎች የህዝብ ቅሬታን በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

"የሚመሰረተው መንግስት የህዝብን ችግር ነቅሶ በማውጣት ማስተካከል ይኖርበታል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ እታፈራሁ ከበደ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

በተለይ ሰላምና ልማትን በዘላቂነት ማስፈንና ማረጋገጥ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመው፣ በየአካባቢው የተጀመሩ የልማት ሥራዎችም ተጠናከርው እንዲቀጥሉ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ ለፌደራል ህዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤቶች አብላጫ የምክር በት ወንበር ማግኙተ መግለጹ ይታወሳል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም