የመስኖ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን አርሶ አደር ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ዓመቱን ሙሉ ለማምረት አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
የመስኖ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን አርሶ አደር ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ዓመቱን ሙሉ ለማምረት አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል
መተማ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ በምእራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ በኩመር አፍጥጥ ቀበሌ ግንባታው የተጀመረው የመስኖ ፕሮጀክት የአካባቢውን አርሶ አደር ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ዓመቱን ሙሉ ለማምረት አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥር የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
በዞኑ የአካባቢውን ማህበረሰብ ዘላቂ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የመስኖ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ዛሬ ተካሄዷል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይም የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አንዳርጌ ጌጡ እንደገለጹት፤ የመስኖ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን አርሶ አደር ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ዓመቱን ሙሉ ለማምረት አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል።
ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን በምግብ ራስን የመቻል፣ ለኢንዱስትሪና ለወጭ ንግድ የሚሆን ትርፍ የማምረት ግብን ለማሳካት አበርክቶው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
በ52 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው የመስኖ ፕሮጀክቱ ከ25 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ በጥራት ተገንብቶ እንዲጠናቀቅም የአካባቢው ማህበረሰብና የወረዳው አስተዳደር የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የመተማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግዛት ሰረፀ በበኩላቸው፤ ለፕሮጀክቱ መተግበሪያ የሚሆን በጀት አስቀድሞ የተያዘ በመሆኑ ግንባታውን በፍጥነት ለማከናወን ያስችላል ብለዋል።
ከመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቱ ጎን ለጎንም የአካባቢውን አርሶ አደሮች በማደራጀት ፈጥነው ወደ ልማት እንዲገቡ በማድረግ ለሌሎች አካባቢዎች የልማት ሞዴል እንዲሆኑ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በፀሐይ ኃይል (ሶላር ኢነርጂ) የሚንቀሳቀሰውን የመስኖ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜና ጥራት ገንብቶ በፍጥነት ለማጠናቀቅ ይሰራል ያሉት ደግሞ የተቋራጩ ስራ አስኪያጅ ደምመላሽ ወርቁ ናቸው።
ለግንባታው መፋጠን የአካባቢው ማህበረሰብና አስተዳደር ሰላሙን በመጠበቅ አጋዥ ሊሆኑ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በወረዳው የኩመር አፍጥጥ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ውበት መኮንን እንደገለፁት፤ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስ ወንዝ ቢኖርም የመስኖ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ በመስኖ ስራው ውጤታማ ሳይሆኑ ቆይተዋል።
አሁን ላይ የመስኖ ግድብ መገንባቱ ከመኸር ልማቱ በተጨማሪ በበጋው ወቅትና ዓመቱን ሙሉ በማልማት ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በዕለቱ የዞንና የወረዳ አመራሮች በተገኙበት ከተቋራጩ ጋር የውል ስምምነት ሰነድና የሳይት ርክክብ በይፋ ተፈጽሟል።