ቀጥታ፡

የምንገነባው መኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን ክብራችንን የሚያስጠብቅ ምቹና ፅዱ አካባቢን ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የምንገነባው መኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን ክብራችንን የሚያስጠብቅ ምቹና ፅዱ አካባቢን ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልዕክታቸው፤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የዛሬ ሁለት ወር የተጀመረው የቅጠል ተራ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት በአስደናቂ ፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከንቲባዋ ዛሬ በሳይቱ በመገኘት የግንባታውን ሂደት የገመገሙ ሲሆን፣ የዛሬ ሁለት ወር የተጀመሩት ህንጻዎች በአሁኑ ወቅት 9ኛ ወለል ላይ መድረሳቸውን ተመልክተዋል።


 

ከቦታ ማጽዳት ስራዎች ጋር በተያያዘ የዛሬ ወር የተጀመሩት ህንጻዎች 4ኛ እና 5ኛ ወለል ላይ የደረሱ ሲሆን፣ ከሁለት ሳምንት በፊት የግንባታ ሂደቱን ከተመለከቱ በኋላ አዲስ የተጨመሩት የሶስት ህንጻዎች ጅማሮም በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በእነዚህ ፕሮጀክቶች የሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ ለንግድ፣ ለጸጥታ፣ ለትምህርት ቤት እና ለጤና ተቋማት፣ ለስፖርት ማዘዉተሪያ፣ ለህፃናት መጫወቻ እና ለሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች እንዲሁም ለህዝብ የጋራ መገልገያዎች እኩል ትኩረት መሰጠቱን ነው ያብራሩት።

በመሆኑም እየተገነባ ያለው መኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን ህጻናት ቦርቀው የሚያድጉበት፣ ወጣቶች የአካልና የአዕምሮ ብቃታቸውን የሚያዳብሩበት፣ ዜጎች አገልግሎቶችን በቅርበት የሚያገኙበት እና ክብራቸውን የሚያስጠብቅ ምቹና ፅዱ አካባቢ መሆኑን አመልክተዋል።

በአጠቃላይ የቅጠል ተራ መኖሪያ መንደርን ትናንት ከተጀመረው የገዳም ሰፈር እና በመሀሉ ላይ ከሚገኘው የጣልያን ሰፈር ጋር በማገናኘትና በማልማት፣ አካባቢውን የዘመነ አኗኗርና ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር ስፍራ ለማድረግ መታቀዱንም ነው የገለጹት።

ከንቲባዋ አክለውም በምርጫ ወቅት ላይ ሆኖ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሳይቀዛቀዝ መቀጠሉ፣ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ነዋሪዎችን በታማኝነት የማገልገል አቋማቸው ፅኑ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

ህንጻዎቹን በጥራት እና በፍጥነት ገንብተው በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ሌት ተቀን እየሰሩ የሚገኙ አመራሮችን፣ ሰራተኞችን፣ ማህበራትን፣ ተቋራጮችን እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም