ቀጥታ፡

በክልሉ ቡናን በክላስተር በማምረት ጥራቱንና የማሳ ሽፋኑን የማሳደግ ስራ እየተከናወነ ነው- ባለስልጣኑ

ሃዋሳ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ቡናን በክላስተር በማምረት ጥራቱንና የማሳ ሽፋኑን የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ቡና ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ቡናን በክላስተር በማምረት  የማሳ ሽፋን እና ጥራቱን የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

ለአብነትም በ2015 ዓ.ም በ25 ክላስተሮች የተጀመረው ቡናን የማልማት ስራ አሁን ላይ ወደ 239 ለማሳደግ  መቻሉን ገልፀዋል።

በዘንድሮው ዓመትም በእያንዳንዱ ቀበሌ ሁለት ሁለት ክላስተሮችን እንዲኖሩ በማድረግ ቡናን የማልማት ስራን ከፍ የማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቡና ማሳን ለማስፋት በየአመቱ የችግኝ ተከላ እንደሚካሄድ የገለጹት ዳይሬክተሩ በዘንድሮ ዓመት 36 ነጥብ 5 ሚሊዮን የቡና ችግኝ መተከሉን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት የቡና ምርታማነት ማሻሻያ ፓኬጆችን ተግባራዊ በማድረግ በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳሪ ለመሆን እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በዘንድሮ ዓመት 31 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የሚገኙ ያረጁ ቡናዎች የማደስ ስራ መሰራቱንም ነው ያነሱት።

በተለይም በክልሉ የሚመረተው ቡና ተፈጥሯዊ ጣእሙን የጠበቀ እንዲሆን የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀትና አጠቃቀም ላይ  እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከቡና ኢንዱስትሪዎች የሚወጣውን የቡና ገለፈት ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት የመቀየር ስራም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም ያጋጥም የነበረውን የአካባቢ ብክለት ከማስቀረት ባሻገር የቡና ጥራትና ምርታማነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና የሚያበረክት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

በክልሉ ያሉ 220 የቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎቹ መደበኛና ቨርሚ ኮምፖስት አዘጋጅተው ለአርሶ አደሩ እንዲያቀርቡ መደረጉንም ነው የተናገሩት፡፡

በማእከላዊ ሲዳማ ዞን የዳሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ባልቻ በላይነህ በበኩላቸው፤ በወረዳው ከሚገኙ 32 ቀበሌዎች ውስጥ ሃያ አንዱ ሙሉ በሙሉ ቡና አምራች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም በወረዳው የቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎችና በተደራጁ ወጣቶች የቡና ጥራት፣ምርታማነትና ተፈጥሮአዊ ጣእም የሚያስጠብቁ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፓስት) እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይሕም ያጋጥም የነበረውን የአካባቢ ብክለት ከመከላከል ባለፈ ቡና ከአርሶ አደሩ ጋር ትስስር ለመፍጠር እና ጥራትን ለማስጠበቅ እያስቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በዳሌ ወረዳ የሾኤ ቀበሌው ሞዴል አርሶ አደር አሰፋ ደበቆ በ 3 ነጥብ 5 ሄክታር ማሳ ላይ ቡና እያለሙ መሆኑን ነው የሚናገሩት ፡፡

የቡና ጥራትና ምርታማነት ለማረጋገጥ ከችግኝ መረጣ እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ በባለሙያ የታገዘ እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ገልጸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ፣ጥላ ዛፍና ደባል ሰብሎችን እንደከተሉ ገልጸዋል፡፡

 

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም