ቀጥታ፡

የወላይታ ሶዶ ከተማ የኮሪደር ልማትን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፡-የወላይታ ሶዶ ከተማ የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የወላይታ ሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የተቀናጀ መሠረተ ልማት አቅርቦት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አስራት ዳዊት ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በከተማዋ በአዲስ መልክ የተጀመረው 4 ኪሎ ሜትር የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራ በልዩ ትኩረት እየተመራ ነው።

የኮሪደር ልማት ሥራው የመኪና፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ እንዲሁም የተለያዩ የመንገድ ዳር ማረፊያዎችንና መዝናኛ ቦታዎችን አካቶ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የኮሪደር ልማቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ምሽትና ቀን የሚሰራው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል። 

አራት ኪሎ ሜትር ለሚሸፍነው የኮሪደር ልማት ከ5ዐዐ ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን የገለጹት አቶ አስራት፣ የግንባታ ሥራው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል፡፡ 

ልማቱ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲበቃ የከተማዋን ውበትና ገጽታ ከማሳደግ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በማሳለጥ ረገድ አበርክቶው የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የኮሪደር ልማቱ የቱሪስት ፍሰትን ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የከተማዋን ገቢ ለማሳደግ ጠቀሜታው ከፍተኛ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተማዋን የኮሪደር ልማት ሥራ እያከናወነ የሚገኘው ወርልድ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ባለቤት አቶ ፍቅሬ ብርሃኔ በበኩላቸው እንዳሉት የኮሪደር ልማቱን በተያዘለት የጊዜ ገድብ ለማጠናቀቅ ምሽትና ቀን እየተሰራ ነው፡፡


 

አስካሁን በኮሪደር ልማቱ ከ200 ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸው፣ ስራውን በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የኮሪደር ልማቱ የሥራ ዕድል እንደፈጠረላቸው የተናገሩት ደግሞ አቶ እሸቱ በዛ እና ወጣት ፈቃዱ መኮንን የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።


 

ሥራው ከቀን ባለፈ ምሽት ጭምር መከናወኑ የሥራ ባህላቸውንእንደቀየረውና ይበልጥ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም