በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተተከሉ ችግኞች የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረጉን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተተከሉ ችግኞች የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረጉን ነው
አዳኝ አገር ጫቆ፣ሰኔ16/2018(ኢዜአ)፡-በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ቀደም ሲል የተተከሉ ችግኞች የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረጓቸው መሆኑን በምዕራብ ጎንደር ዞን የአዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
አርሶ አደሮቹ እንዳሉት ቀደም ሲል በአካባቢያቸው የተከናወኑ የችግኝ ተከላና የእንክብካቤ ሥራዎች የአፈርና የውሃ ሀብትን በመጠበቅ ለአካባቢው ግብርና መነቃቃትና ለተጠቃሚነታቸው ማደግ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
በቀጣይም ይህን ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደገ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል መዘጋጀተቸውን ተናግረዋል።
ከወረዳው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሙሉነህ ጀምበር እንደገለጹት፣ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት በአካባቢያቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ተጠቃሚ አድርጓቸዋል።
ቀደም ሲል በድርቅና በአፈር መሸርሸር ተጎድቶ የነበረው መሬት ማገገሙና የከርሰ ምድር ውሃ መጨመሩ አትክልትና ፍራፍሬ በመስኖ አልምተው ተጠቃሚ ለመሆን እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
ይህን ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግም በመጪው ክረምት በወል መሬት ላይ ከሚተክሉት የደን ችግኞች በተጨማሪ በራሳቸው ግማሽ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ ማንጎና ዘይቱን ለመትከል ችግኝ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ሌላኛው የወረዳው አርሶ አደር ተሾመ ጫንያለው በበኩላቸው እንዳሉት የአረንጓዴ ልማቱ የእንስሳት መኖ ልማት፣ የንብ ማነብና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በማከናወን ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ቀደም ሲል የተከሏቸው ማንጎና ሌሎች የቆላ ፍራፍሬ ችግኞች አሁን ላይ ምርት መስጠት በመጀመራቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደር ታረቀኝ ታከለ በበኩላቸው፣ ዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞችን በማዘጋትና የመትከያ ጉድጓዶችን በወቅቱ በመቆፈር በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በመጀሪያው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከሉት የቡና ችግኝ በአሁኑ ወቅት ምርት መስጠት በመጀመሩ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከምርቱ ሽያጭ ከ70ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ያገኙትን ጥቅም ለማስፋትም በክረምት በሚካሄደው የችግኝ ተከላ በንቃት ለመሳተፍ የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራውን ቀድመው ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፈንታሁን ኪሮስ በበኩላቸው እንዳሉት በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል እየተሰራ ነው።
ባለፈው ዓመት ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን አስታውሰው፣ለእዚህም ማህበረሰቡ ለተተከሉ ችግኞች የሚያደርገው እንክብካቤ እያደገ መምጣት አስተዋጾ አድርጓል ብለዋል።
በዘንድሮ ክረምትም ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የደንና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የቆላ ፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ሰፊ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።
ለተከላ ከተዘጋጁ ችግኞች ውስጥ አካሻ ሰኔጋል፣ ሽመል (የቆላ ቀርቀሃ)፣ ኒም፣ ሞሪንጋ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ እና ሌሎች እንደሚገኙበት የጠቆሙት አቶ ፈንታሁን፣ ለእዚህም ከ200 ሺህ በላይ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል ብለዋል።