ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን ችግር የሚፈቱ የምርምር ሥራዎችን ሊያጠናክር ይገባል

አሰላ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የአርሶ አደሩን ችግር የሚፈቱ የምርምር ሥራዎች ላይ በማተኮር እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲያስቀጥል የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሣ (ዶ/ር) አመለከቱ።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ1 ሺህ 355 በላይ ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ።

በወቅቱም የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሣ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ተመራቂዎች የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አሻራቸውን ማኖር አለባቸው።


 

ተመራቂዎች ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እየተጓዘች ባለችበት ወቅት መመረቃቸው ብዙ ስራ ይጠብቃቸዋል ብለዋል።

ተመራቂዎች የዜጎችን ሕይወት በመቀየር ሂደት ውስጥ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ዩኒቨርሲቲውም የአርሶ አደሩን ችግር በሚፈቱ የምርምር ሥራዎች ላይ በማተኮር እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲያስቀጥል አመልክተዋል።

በተመሳሳይም ጤናን ጨምሮ በማኅበራዊ አገልግሎቶች እያስገኘ ያለውን ውጤታማ የምርምር ሥራዎችና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፍቃዱ ምትኩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።


 

በግብርና፣ በጤና፣ በኢንጂነሪንግና በቴክኖሎጂ ውጤታማ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማከናወን ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ተማሪዎች ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የኢንተርፕረነርሺፕ ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎትን ለማስፋፋት በሠራው ሥራ የእናቶችና ሕፃናት ሆስፒታል ገንብቶ ወደ ሥራ ማስገባቱን ገልጸዋል።

የአሰላ ሪፈራል ሆስፒታልን ጨምሮ ከወረቀት ንክኪ ነጻ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤት ማምጣቱንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም