በአምቦ ወረዳ የሚገኙ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለአካባቢው ማህበረሰብ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት እየሰጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአምቦ ወረዳ የሚገኙ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለአካባቢው ማህበረሰብ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት እየሰጡ ነው
አምቦ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ወረዳ የሚገኙ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለአካባቢው ማህበረሰብ በቅርበት አገልግሎት በመስጠት፣ ህብረተሰቡን ከእንግልትና ከተጨማሪ ወጪ እየታደጉ መሆናቸውን ተገልጋዮች ገለጹ።
ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት የሀገር ሽማግሌ አቶ ከበደ በየንሳ፤ ቀደም ሲል ህብረተሰቡ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን ለመፍታትና ፍትህ ለማግኘት ረጅም ርቀት ይጓዝ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከዚህ ቀደም ፍትህ ለማግኘት ለከፍተኛ ወጪና እንግልት ይዳርጉ እንደነበር ጠቁመው፣ አሁን ላይ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች በአቅራቢያቸው ስራ መጀመራቸው ችግሩን ቀርፎ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኙ ማገዛቸውን ገልጸዋል።
አቶ ከበደ አክለውም፣ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች መቋቋም በተለይም የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን መጨናነቅ ከመቀነሱም በላይ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ጊዜና ገንዘቡን እንዲቆጥብ ትልቅ እገዛ ማድረጉን አስረድተዋል።
ሌላኛዋ የወረዳው ነዋሪ ሃደ ሲንቄ እሸቷ ሚደቅሳ በበኩላቸው፤ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ህብረተሰቡን በቅርበት በማገልገልና አለመግባበት ውስጥ የገቡ ወገኖችን በማስማማት ረገድ የሚሰጡት ፍትህ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሰራሩ የአካባቢውን ባህልና የገዳ ሥነ-ሥርዓትን መሠረት ያደረገ በመሆኑ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከቀን ወደ ቀን እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
የሰደን ሊባን ይግባኝ ሰሚ ባህላዊ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የኦሮሞ አባገዳዎች ኅብረት ሰብሳቢ አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ፤ ፍርድ ቤቱ የአካባቢውን የዳኝነት ባህልና የገዳ ሥነ-ሥርዓት መሠረት በማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት በበጀት ዓመቱ ወደ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ከመጡ መዝገቦች መካከል 96ቱ ውሳኔ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት አገልግሎት የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴቶች ጠብቆ ለማቆየት እንደሚረዳ፣ ፍትህን በአጭር ጊዜና ያለ ምንም ክፍያ ለማቅረብ ተመራጭ መሆናቸውን አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ አብራርተዋል።