ቀጥታ፡

በ 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል

ደሴ፤ ሰኔ 16/ 2018 (ኢዜአ)፡-በዘንድሮ ዓመት በሚካሔደው 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት ማድረጋቸውን በደሴ ከተማ የሚገኙ ተፈታኝ ተማሪዎች ገለፁ።

በከተማዋ ከ2 ሺህ 800  በላይ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንደሚወስዱ የከተማው ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።

ተማሪ ቀመርያ ከማል  በደሴ ከተማ የሆጤ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፤ በብሔራዊ ፈተናው የላቀ ውጤት በማምጣት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመግባት ዝግጅት ማድረጓን ለኢዜአ ገልፃለች።

ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ የነበረውን ትምህርት በመከለስና የተጠናከረ ጥናት በማድረግ የፈተናውን እለት እየተጠባበቀች እንደምትገኝ ነው የምትገልፀው።

በትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ስራው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ ጭምር መካሔዱ ለፈተናው በተሻለ ሁኔታ እንድዘጋጅ አድርጎኛል የምትለው ደግሞ ሌላዋ የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችው ፅዮን ግርማ ነች ።

"ጊዜዬን በአግባቡ በመጠቀም  በትጋት እየተዘጋጀሁ ነው" ያለችው ጽዮን ፈተናውን ተረጋግቶ  በመስራት ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ትኩረት ሰጥቼ  እየተዘጋጀሁ ነው ብላለች።

የመምህር አካለ ወልድ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሰሚራ ክንዱ ፤በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናው የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ተወዳዳሪ ለመሆን በቂ ዝግጅት ማድረጓን ነው የገለፀችው ።

የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ  የምትፈልገው ቦታ ላይ ለመድረስ የራስ ጥረት ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ሌት ተቀን ጥረት እያደረገች መሆኑዋንም ነው የምትናገረው።


 

የሆጤ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ጌታቸው መከተ በበኩላቸው፣ በዘንድሮውዓመት ትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ላይ የሚያስቀምጣቸው ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

ለተፈታኞች ቤተ መጽሕፍቶችና ቤተ ሙከራዎችን  የስራ ሰዓታቸውን ጭምር ከማራዘም ባለፈ የማካካሻ ትምህርትን በመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅር አበበ በበኩላቸው፣ በከተማው 2 ሺህ 854 ተማሪዎችን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና  እንደሚወስዱ ገልፀዋል።


 

ተማሪዎቹ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡም ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም