ቀጥታ፡

ዘላቂ ለውጥ የሚመጣው በጋራ በመቆም ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018(ኢዜአ) ፦ ‎ሀገርን መገንባት በአንድ ትውልድ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን የሁላችንም የጋራና ቀጣይነት ያለው ሥራ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

‎“ኢትዮጵያ ታከናውናለች” የተሰኘ ብሔራዊ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሔደ ይገኛል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ‎“ኢትዮጵያ ታከናውናለች” በተሰኘው ብሔራዊ ጉባኤ ላይ በመገኘቴ ታላቅ ክብር ይሰማኛል ሲሉ ገልጸዋል።

‎“ከለውጥ ወደ ዘላቂ ሽግግር” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው ጉባኤ ላይ፣ በየደረጃው የተጓዝንበትንና አሁን የደረስንበትን መንገድ መለስ ብዬ እንድቃኘው አድርጎኛል ሲሉም ገልጸዋል።

ሀገራችን በራሷ አቅም ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመገንባት፣ ያልተሞከሩ ግዙፍ ልማቶችን በማከናወን በየጊዜው ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረች ትገኛለች ብለዋል።

እነዚህ ሁሉ በአጋጣሚ የተገኙ ድሎች አይደሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመደመር መንፈስ ላይ ተመስርተው፣ ዘላቂ ለውጥ የሚመጣው በጋራ በመቆም ነው በሚል ጽኑ እምነት የተወሰዱ በቆራጥ ውሳኔዎች የተገኙ ውጤቶች ናቸው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ‎የጀመርናቸው ለውጦች በራሳቸው የመጨረሻ ግብ አይደሉም ይልቁንም ከእኛ በኋላ ለሚመጡት ተከታታይ ትውልዶች የምንጥለው ጠንካራ መሠረት ነው ብለዋል።

‎ሀገርን መገንባት በአንድ ትውልድ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን የሁላችንም የጋራና ቀጣይነት ያለው ሥራ በመሆኑ፤ በዚህ ጽኑ እምነት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይህንን መንፈስ ይዞ ወደፊት እንዲጓዝ፣ የተቀበለውን ወረት አግዝፎ ይበልጥ ወደ ላቀ ከፍታ እንዲያመራ ጥሪዬን አቀርባለሁ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም