ቀጥታ፡

ብልፅግና ፓርቲ በገባው ቃል መሰረት የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል አለበት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ በገባው ቃል መሰረት የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለፁ።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች ብልፅግና ፓርቲ አብላጫውን መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል።

አስተያየታቸው ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ ፓርቲው ከምርጫው በፊት ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመራቸውን የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች በቀጣይም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ተቋማትን በአንድ ቦታ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ብልሹ አሠራርን ለማስቀረት የተገበረውን የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ማስፋት እንዳለበት ነው ሀሳባቸውን የሰጡት።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ማናዬ ዘነበ እንዳሉት፤ ፓርቲው የሚታይና የሚጨበጥ ስራ በማከናወኑ በርካታ ሕዝብ በድምጹ መርጦታል ይላሉ።

አብላጫ ድምፅ ያገኘው ፓርቲ የተሰጠውን ኃላፊነት ግምት ውስጥ በማስገባት በቀጣይ የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ብሩክ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ፓርቲው ካሁን ቀደም በኮሪደር ልማትና በወንዝ ዳርቻ የጀመራቸው የልማት ሥራዎች መዲናዋን ሙሉ ለሙሉ የቀየሩ በመሆናቸው ሊጠናከሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ሕዝቡም ካሁን ቀደም ያሳየውን አጋርነት በማጠናከር ከመንግስት ጎን በመቆም ለተሻለች ኢትዮጵያ በጋራ ልንሠራ ይገባል ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ማሸነፉን ተከትሎ፣ ከምርጫ በፊት ለህዝብ የገባውን ቃል ወደ መሬት ማውረድና በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል ያሉት ደግሞ ከበቡሽ ሽምብር ናቸው። 

የሕዝብ አመኔታን ለማጽናት እና የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት በማረጋገጥ ሕዝቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ሥራዎች በትኩረት ሊያከናውን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩትን እንደ ስንዴ ልማትና የሌማት ትሩፋት ያሉ ሥራዎችን ይበልጥ በማስፋት  በምግብ ራስን የመቻል ግብን ማረጋገጥና የሸቀጦችን አቅርቦት ማሳደግ እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ዮሴፍ ታመነ በበኩሉ የምርጫው አሸናፊ ብልፅግና ፓርቲ ከምርጫው በፊት ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ሲያከናውን መቆየቱ ገልፆ በቀጣይም ይህንኑ ሊያጠናክር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም ወጣቱ  የልማት ተሳታፊና የስራ እድል ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አንስተዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ውበት ደጉ ፥ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ የተመረጠው ፓርቲ ካሁን ቀደም በተለይም ለወጣቶች ተስፋ ሰጪ የሆኑ ሥራዎች ሲያከናውን መቆየቱን ገልፃ በቀጣይም በላቀ ትጋት ሊሠራ ይገባል ነው ያለችው።

የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ የአምራች ዘርፍና ሌሎችም የልማት ፕሮጀክቶችን ማስፋት እንዳለበትም በመጠቆም፥ ፓርቲው የገባውን ቃል በአግባቡ እንዲፈጽም አጋዥ ሚና እንወጣለን ብላለች።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም