በምዕራብ ወለጋ ዞን ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ67 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ዝግጁ ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋ ዞን ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ67 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ዝግጁ ሆኗል
ጊምቢ፣ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ67 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ዝግጁ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፍቅሩ ብርሃኑ፤ በዞኑ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኞችም ሆነ የመሬት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በበጋ ወቅት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማቶችን ጨምሮ በተመረጡ ከ67 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች ተመናምኖ የነበረውን የደን ሽፋን ከመመለሱ በላይ፣ ለብዝሃ ሕይወት ምቹ አካባቢ መፍጠር ማስቻሉን ተናግረዋል።
በተለይም የመሬት ለምነትን ጠብቆ በማቆየትና የቡናና የሰብል ምርት መጠንን በማሻሻል የተራቆቱ አካባቢዎች ዳግም ወደ ለምነታቸው እየተመለሱ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ለእንስሳት እርባታ፣ ለንብ ማነብ፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ምቹ ሥነ-ምህዳር ከመፍጠርም ባለፈ በርካታ ወገኖችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከማድረግ ረገድ አበርክቶው የጎላ እንደነበረ ገልጸዋል።
የዞኑ አርሶ አደሮች ባዩት ለውጥ በመነሳሳት በየዓመቱ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በስፋት የማዘጋጀት ባህል ከማዳበር ባሻገር ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እያስቻላቸው መሆኑንም አብራርተዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች ከ328 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ ፍቅሩ ጠቁመዋል።
ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ አፕልና ለሌሎች የደን ሽፋን የሚውሉ በርካታ ችግኞች መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።
የችግኝ ማፍላት ሥራው በመንግሥት፣ በግል እና በማህበራት አማካኝነት መካሄዱን አንስተዋል።
ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ለተከላው 293 ሚሊዮን ጉድጓድ መዘጋጀቱንና፤ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን በማሳተፍ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።