ቀጥታ፡

የመዲናዋ ነዋሪ ኃላፊነቱን በመወጣት አካባቢውን ከጎርፍ አደጋ ሊጠብቅ ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፡- የከተማችን ነዋሪዎች የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን በማፅዳትና ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ አካባቢያችሁን ከጎርፍ አደጋ ልትጠብቁ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ።

ከንቲባ አዳነች በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በአቃቂ ቃሊቲ ብዙ ጊዜ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆነው ቦታ ላይ ጎርፍን የመከላከልና የአደጋ ዝግጁነት ሥራን በይፋ አስጀምረናል ብለዋል።

አቃቂ ቃሊቲ በተፈጥሯዊ አቀማመጡ የአዲስ አበባ የታችኛው ክፍል በመሆኑ፤ ከዚህ በፊት በጎርፍ አደጋ በተደጋጋሚ ተጠቂ ሲሆን መቆየቱንም አውስተዋል።


 

በዛሬው ዕለትም ለዚህ አካባቢ ቅድሚያ በመስጠት በሁሉም የከተማችን ቦታዎች ላይ ወንዞች ተፈጥሯዊ ፍሰታቸውን ጠብቀው እንዲፈስሱ የተለያዩ ግንባታዎችን የመሥራትና የፍሳሽ መስመሮችን የማፅዳት ንቅናቄን አስቀጥለናል ሲሉም አስታውቀዋል።

ውድ የከተማችን ነዋሪዎችም አሥተዳደራችን እየሠራ ባለው የመከላከልና አደጋ እንዳያጋጥም የቅድመ ዝግጁት ሥራ ላይ በንቃት ተሳተፉ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

አክለውም፤ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን በማፅዳትና ቆሻሻን ወደ ፍሳሽ መውረጃ ባለመጣልና በአግባቡ በማስወገድ አካባቢያችሁን ከጎርፍ አደጋ ጠብቁ ሲሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም