በአዲስ አበባ የ2018 የክረምት ጎርፍ መከላከል እና የአደጋ ዝግጁነት ንቅናቄ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የ2018 የክረምት ጎርፍ መከላከል እና የአደጋ ዝግጁነት ንቅናቄ ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የ2018 ክረምት ጎርፍ መከላከል እና የአደጋ ዝግጁነት ንቅናቄ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ፤ ንቅናቄው ክረምቱን ተከትሎ በሰው እና ንብረት ላይ ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ መከላከልን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም የአደጋ ተጋላጭነትን በአግባቡ አጥንቶ ዘላቂ መፍትሔ ሲሰጥ መቆየቱን አመላክተዋል።
በዚህም ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ወንዞች የንጹህ ውሃ መውረጃ እንጂ የሰው ህይዎት የአደጋ መንስዔ ሊሆኑ እንደማይገባ አመልክተው፤ በቀጣይ ወንዞች የአደጋ መንስኤ እንዳይሆኑ በወንዝ ዳርቻ ልማት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በምከትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው፤ በመዲናዋ ከአደጋ ተጋላጭነት ነጻ ከባቢን ለመፍጠር ሰፋፊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም ከዚህ ቀደም የአደጋ መንስዔ የነበሩ አካባቢዎች ወደ ምቹና ተመራጭ የመኖሪያ ስፍራነት መቀየራቸውን አመላክተዋል።
በቀጣይም ከተማዋን ምቹ እና ለኑሮ ተመራጭ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።