ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ ጠንካራ ርዕይና አመርቂ አፈጻጸም አላት-ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ ጠንካራ ርዕይና አመርቂ አፈጻጸም እንዳላት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ32 ተሰያሚ ፕሬዚዳንት የሆኑት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

ቻተም ሃውስ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም በለንደን ያዘጋጀውና “በተከፋፈለ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ የኮፕ ጉባኤዎችን አስፈላጊነት ማጉላት” በሚል ርዕስ በተካሄደው የአየር ንብረት ሳምንት የውይይት መድረክ ላይ ተካሂዷል።


 

በመድረኩም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ32 ተሰያሚ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣የኮፕ30 ፕሬዚዳንት አንድሬ ኮሬያ ከብራዚል እንዲሁም የኮፕ31ን የወከሉት የቱርክ የአካባቢ፣ የከተማ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር በ‎ውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ ያላትን ጠንካራ ርዕይ እና አመርቂ አፈጻጸም አንስተዋል።

በተለይም ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ በፖሊሲ ተደግፈው ተግባራዊ የተደረጉ አፈጻጸሞችን አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።


 

የኮፕ32 ተሰያሚ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ አክለውም፥ ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው የኮፕ32 ቀዳሚ ተግባራት፣በቱርክና አውስትራሊያ በጋራ ከሚዘጋጀው የኮፕ31 የተገኙ ውጤቶች በመነሳት፣ ቀጣይነትን ማረጋገጥ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ይህ አካሄድም ከኢትዮጵያ በፊት የኮፕ ጉባኤዎችን ካዘጋጁት ጋር በቅንጅት በመስራት፣ የጋራ ተግባራትን ማጠናከር መሆኑን ጠቁመዋል።

እንዱሁም በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ሂደት ላይ ያለውን ተስፋ መልሶ ማቀጣጠል የሚለውን የ“መደመር” መርህ እንደሚያንጸባርቅ አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም