ሀኪም ጋራ ኢኒሼቲቭን በመደመር መንግስት እይታ በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው -ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
ሀኪም ጋራ ኢኒሼቲቭን በመደመር መንግስት እይታ በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው -ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018(ኢዜአ) ፦ በሀረር ከተማ የተጀመረው ሀኪም ጋራ ኢኒሼቲቭ በመደመር መንግስት እይታ ጥራትና ፍጥነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በሀረር ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን የሀኪም ጋራ ኢኒሼቲቭን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በመስክ ምልከታው ላይም ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለፁት በአው ሀኪም ተራራ ላይ እየተሰራ የሚገኘው ኢኒሼቲቩ የአዲሲቷ ሀረር አለም አቀፍ ምልክት ከመሆን ባሻገር ለክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ እድገት ጉልህ ፋይዳ ያበረክታል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም ለቱሪዝም መዳረሻነትና ለህዝብ መዝናኛነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የፕሮጀክቱ እውን መሆን የጎብኚዎችን ቆይታ በመጨመር ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አንፃርም ሚናው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱም 1ሺህ 870 ደረጃዎች እንደሚኖሩት እና ሁለት ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የመሰረተ ልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ አካባቢያዊ ሀብቶችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ተራራው ራሱን የቻለ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው በማድረግ ተገቢው ጥበቃ እንደሚደረግለት አመላክተው ለዚህም ህገ-ወጥ ግንባታ በመከላከል ረገድ በቅንጅት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተራራውን አረንጓዴ የማልበስ ስራ ይሰራል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜና ጥራት ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመው ለዚህም የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ ነው የተናገሩት።