በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች የኮሪደር ልማትና ሌሎች ፕሮጀክቶች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች የኮሪደር ልማትና ሌሎች ፕሮጀክቶች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች የኮሪደር ልማትና ሌሎች ፕሮጀክቶች ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ እድል መፍጠራቸውን የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ተጀምሮ የከተማ ገጽታን በመቀየርና የነዋሪዎችን ህይወት በማዘመን ረገድ አንጸባራቂ ውጤት የተመዘገበበት የኮሪደር ልማት አሁን ላይ ወደ ክልል ከተሞች ተስፋፍቶ ቀጥሏል፡፡
በአዲስ አበባ እንደታየው ሁሉ በክልል ከተሞች የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መስመሮች፣ የንግድና የሕዝብ መዝናኛ ሥፍራዎች ደረጃቸውን ጠብቀው ተገንብተዋል፡፡
ይህም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድልን የፈጠረው የልማት ሥራ የከተሞችን ውበት እና ለኑሮ ያላቸውን ምቾት በእጅጉ እየጨመረው ይገኛል።
የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተሞች የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ ያሉ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለወጣቱ ሰፊና ዘላቂ የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አስፋው ለገሰ፤ ኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሜጋ ፕሮጀክቶች በርካታ ዜጎችን በሥራ ዕድልና በንግድ ሥራ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
በከተማዋ በተከናወኑ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የፓርኮች ግንባታ እና የቤት ልማት ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡
ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት እስካሁን ድረስ ከ365 ሺህ በላይ ዜጎች በተለያዩ መስኮች ወደ ሥራ መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ ኢንዱስትሪ፣ ኮንስትራክሽን፣ የከተማ ግብርና፣ አገልግሎት በስፋት የሥራ ዕድል የተፈጠረባቸው የሥራ መስኮች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሮቤል ጌታቸው በበኩላቸው፣ ከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ እስካሁን ለ19 ሺህ 642 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህም በከተማዋ የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ ያሉ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ጉልህ ድርሻ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡