ቀጥታ፡

የምርጫ አሸናፊው ብልጽግና ፓርቲ ለህዝብ የገባውን ቃል ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ልማትን ሊያረጋግጥ ይገባል

ጋምቤላ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፡-በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አሸናፊ የሆነው የብልጽግና ፓርቲ ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር በመተርጎም ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ በትጋት መስራት እንዳለበት የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተደረገው ለሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።

የምርጫውን ውጤት በማስመልከት የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በ7ኛው ጠቅላላ የምርጫ አሸናፊው ብልጽግና ፓርቲ የገባውን ቃል ተግባራዊ በማድረግ ለህዝቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሊተጋ ይገባል ብለዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አንዳርጌ ዋሲሁን፤አሸናፊው ፓርቲ በማኒፌስቶውና በፕሮግራሙ ለህዝብ የገባውን ቃል ተግባራዊ በማድረግ በህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ህዝቡም ከመንግስት ጎን በመሆን በምርጫው ያሳየው ተሳትፎ በልማቱ ለመድገም አብሮነቱን በማጠናከር በአንድነት ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል።


 

በሀገራዊ ምርጫው አሸናፊ የሆነው የብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማስቀጠል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል ያለው ደግሞ ወጣት ኡሞድ ኡሞድ ነው።

በተለይም እንደ ጋምቤላ ክልል ባለፉት ዓመታት የታዩት የልማት ጅማሮዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንሻለን ለዚህም ከመንግስት ጎን እንቆማለን ብለዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዘለቀ ደበሌ በሰጡት አስተያየት አሸናፊው ፓርቲ የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን የማረጋገጥ ስራው ትኩረቱ ሊሆን ይገባል ብለዋል።


 

ፓርቲው በቀጣይ አምስት ዓመታት የህዝቦችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት ጊዜ ሊሆን ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በፓርቲው ማኒፌስቶና ፕሮግራሞች ለህዝቡ የተገለጹ እቅዶችን ተግባራዊ በማድረግ ተጨባጭ የልማት ውጤት ለማስመዝገብ ሊሰራ ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ካማ ኡቦንግ ነው።


 

የብልጽግና ፓርቲ በምርጫው ማሸነፉ ቀደም ሲል የጀመራቸውን ስራዎች ስኬታማ ለማድረግ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል ያለው ወጣቱ፤ እኛም እንደ ወጣት ከጎኑ ሆነን እንተጋለን ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም