ቀጥታ፡

ጋና ከእንግሊዝ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከኮሎምቢያ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የ12ኛ ቀን ውሎ የምድብ 11 እና 12 ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

በምድብ 12 እንግሊዝ ከጋና ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በቦስተን ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ እንግሊዝ ክሮሺያን 4 ለ 2፣ ጋና ፓናማን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።

ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

እ.አ.አ በ2011 በዌምብሌይ ስታዲየም ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ አንድ አቻ የተለያዩበት ውጤት ብቸኛ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ነው።

በዛሬው ጨዋታ እንግሊዝ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን ብትወስድም ጋና ጠንካራ ፉክክር ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።

አሸናፊው ሀገር ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቱን ያረጋግጣል።

በዚሁ ምድብ ሌላኛው መርሐ ግብር ፓናማ ከክሮሺያ በቶርንቶ ስታዲየም ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸው ሽንፈት ያስተናገዱት ሁለቱ ሀገራት በውድድሩ ላይ ለመቆየት ከዛሬው ጨዋታ ሶስት ነጥብ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

በምድብ 11 ኮሎምቢያ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከሌሊቱ 11 ሰዓት በጓድላሃራ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ኮሎምቢያ ኡዝቤኪስታንን 3 ለ 1 በመርታት ዓለም ዋንጫውን በድል የጀመረች ሲሆን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከፖርቹጋል አንድ አቻ ተለያይታለች።

ከ52 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫው የተመለሰችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመጀመሪያ ዓለም ዋንጫ ጎሏን በአሮን ዊሳ አማካኝነት አግኝታለች። በውድድሩ የመጀመሪያ ነጥቧን አስመዝግባለች።

የማዕከላዊ አፍሪካ ሀገር ወደ ጥሎ ማለፉ የመግባት እድሏን የዛሬውን ጨዋታ በድል መወጣት ይኖርባታል።

ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።




በዚሁ ምድብ ፖርቹጋል ከኡዝቤኪስታን ጋር ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ በሂውስተን ስታዲየም ጨዋታዋን ታከናውናለች።

ፖርቹጋል ከመጀመሪያው ጨዋታ የአቻ ውጤት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ትፋለማለች። የማሸነፍ ሰፊ የቅድሚያ ግምትም አግኝታለች።

በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን እያደረገች የምትገኘው ኡዝቤኪስታን ከሽንፈት አገግማ ድል የማስመዝገብ ከባድ የቤት ስራ ይጠብቃታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም