ፈረንሳይ እና ኖርዌይ ጥሎ ማለፉን መቀላቀላቸውን አረጋገጡ - ኢዜአ አማርኛ
ፈረንሳይ እና ኖርዌይ ጥሎ ማለፉን መቀላቀላቸውን አረጋገጡ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የምድብ ዘጠኝ ሁለተኛ ጨዋታዎች ከእኩለ ሌሊት በኋላ ተደርገዋል።
በኒው ዮርክ ኒው ጀርዚ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኖርዌይ ሴኔጋልን 3 ለ 2 አሸንፋለች።
አርሊንግ ሃላንድ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ማርከስ ሆልምግሬን ፔደርሰን ቀሪዋን ጎል ለኖርውይ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ኢስማኤላ ሳር ለሴኔጋል ግቦቹን አስቆጥሯል።
በጨዋታው ሴኔጋል የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ብትወስድም ኖርዌይ የግብ እድሎችን በመፍጠር ተሽላ ተገኝታለች።
በመጀመሪያ የዓለም ዋንጫው እየተሳተፋ የሚገኘው አርሊንግ ሃላንድ በውድድሱ ላይ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት አራት አድርሷል።
ሃላንድ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
ውጤቱን ተከትሎ ኖርዌይ ወደ ጥሎ ማለፍ (32 ውስጥ) አልፋለች።
በውድድሩ ሁለተኛ ሽንፈቷን ያስተናገደችው ሴኔጋል በሂሳባዊ ስሌት ወደ ጥሎ ማለፉ ምርጥ ሶስተኛ ሆኖ መግባት በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ ኢራቅን ማሸነፍ ይጠበቅባታል።
በዚሁ ምድብ በፊላደልፊያ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፈረንሳይ ኢራቅን 3 ለ 0 አሸንፋለች።
ኪሊያን ምባፔ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ኡስማን ደምቤሌ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ምባፔ በዓለም ዋንጫው በአጠቃላይ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት 16 በማድረስ ከጀርመኑ ሚሮስላቭ ክሎዝ (16) እኩል በመሆን ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
18 ግቦች ካስቆጠረው የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ በሁለት ጎል ዝቅ ብሎ ይገኛል።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛትም አራት አድርሷል።
ምባፔ ለፈረንሳይ 100ኛ ጨዋታውን ያደረገ ሲሆን 59 ግቦችን በማስቆጠር የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን አጠናክሯል።
የጨዋታው ኮከብ በመባል ተመርጧል።
በመብረቅ እና በመጥፎ የአየር ንብረት ምክንያት ለሁለት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ተቋርጦ በነበረው ጨዋታ ፊረንሳይ ብልጫ ወስዳ ተጫውታለች።
ውጤቱን ተከትሎ ፈረንሳይ በስድስት ነጥብ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።
በምድቡ ሁለተኛ ሽንፈቷን ያስተናገደችው ኢራቅ ምርጥ ሶስተኛ ሆኖ የማለፍ እድሏን ለመጠቀም ሴኔጋልን በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባታል።
ፈረንሳይ ከኖርዌይ፣ ሴኔጋል ከኢራቅ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ናቸው።