ቀጥታ፡

ሜሲ የዓለም ዋንጫን የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብረ ወሰን በሰበረበት ጨዋታ አርጀንቲና ጥሎ ማለፉን ተቀላቀለች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የምድብ 10 መርሐ ግብር አርጀንቲና ኦስትሪያን 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ማምሻውን በዳላስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሊዮኔል ሜሲ በ38ኛው እና በ95ኛው ደቂቃ ግቦቹን አስቆጥሯል።

ሜሲ በዓለም ዋንጫው ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 18 በማድረስ የምንጊዜም  ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ክብረ ወሰን ከጀርመኑ ሚሮስላቭ ክሎዝ (16 ጎል) ተረክቧል።

ሜሲ በስምንተኛው ደቂቃ ቡድኑ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ስቷል።

የ38 ዓመቱ ተጫዋች በአጠቃላይ ለሀገሩ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት 122 በማድረስ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን አጠናክሯል።

ውጤቱን ተከትሎ የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ አርጀንቲና በስድስት ነጥብ ወደ ጥሎ ማለፍ ገብታለች። 

ኦስትሪያ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በዚሁ ምድብ ጆርዳን ከአልጄሪያ በሳንፍራንሲስኮ ቤይ ኤሪያ ስታዲየም ከማለዳው 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሁለቱ ሀገራት በመጀመሪያ ጨዋታቸው ሽንፈት አስተናግደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም