ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የፍየልና በግ የእንስሳት ሃብቶች ምርታማነት የማሳደግ የዝርያ ማሻሻል ሥራ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ):- የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የፍየልና በግ የእንስሳት ሃብት ዝርያን የሚያሻሽሉ ሙያተኞችን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።


በዚህም ኢንስቲትዩቱ ከሰኔ 08 እስከ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በሰው ሰራሽ ማዳቀል የፍየልና በግ የእንስሳት ሃብት ዝርያን ለማሻሻል ለሙያተኞች የሰጠውን ስልጠና በማጠናቀቅ ሰልጣኞችን  አስመርቋል።

የግብርና ሚንስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት ያላት ሀገር ናት ብለዋል።

የኢትዮጵያን የፍየልና በግ የእንስሳት ሃብት ምርታማነትን ለማሻሻልም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችንና የአሰራር ሥርዓቶችን በመቅረፅ እየተሰራባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የፍየልና በግ የእንስሳት ሃብት ምርታማነትን ለማሻሻል እየተሰራበት የሚገኘው የሰው ሰራሽ ማዳቀል ሥነ-ዘዴ ተጨባጭ ውጤት እየተገኘ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩትም የሰው ሰራሽ ማዳቀል ሙያተኞችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት መሰረት መጣሉን አንስተዋል።

በኢንስቲትዩቱ ትምህርትና ስልጠና የተሰጣቸው ሙያተኞችም የእንስሳት ሃብት ምርታማነትን በማሻሻል ህዝባቸውን ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስራት ጤራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት የገጠር ሽግግርን ለማሳለጥ ለእንስሳት ሃብት ምርታማነት ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በዚህም የመንግሥትን መርህ ታሳቢ በማድረግ በሰው ሰራሽ የማዳቀል ሥነ-ዘዴ የፍየልና በግ የእንስሳት ሃብት ምርታማነትና ጤንነት ሙያተኞችን እያሰለጠነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለምርቃት ለበቁት ሰልጣኝ ሙያተኞችም በእንስሳት እንክብካቤና አመጋገብ፣ በሽታ መከላከልና ጤና አጠባበቅ፣ ምርት ማቀነባበሪያና የገበያ ትስስር ትምህርት መሰጠቱን አስረድተዋል።

በስልጠናውም የያቤሎ፣ ጂንካ፣ ባኮ፣ አዳሚቱሉ፣ የዓርባ ምንጭ ምርምር ማዕከላት፣ የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት እንዲሁም የግል እርሻ  ሙያተኞች መሳተፋቸውን አስረድተዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም