ባለስልጣኑ የትምህርት ኢንስፔክሽን አገልግሎት ተደራሽነቱን ማስፋፋትና አቅሙን ማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ባለስልጣኑ የትምህርት ኢንስፔክሽን አገልግሎት ተደራሽነቱን ማስፋፋትና አቅሙን ማጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የትምህርት ኢንስፔክሽን አገልግሎት ተደራሽነቱን ማስፋፋትና አቅሙን ማጠናከር እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የ2018 በጀት ዓመት የአስራ አንድ ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ባለስልጣኑ ዓለም አቀፍ እውቅናን ለማግኘት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትና ሌሎች ሥራዎች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ጠይቀዋል፡፡
የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አሕመድ አብተው (ዶ/ር) ባለፉት ዓመታት የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተከናወኑ ተግባራት የትምህርት ተቋማት ጥራት ላይ ሰፊ ለውጥ መመዝገቡን አመላክተዋል፡፡
የአካዳሚክ ጥራት ኦዲት፣ የክትትልና ቁጥጥር፣ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ፣ የአቻ ግመታ መመሪያዎችና ስታንዳርዶች ሥራ ላይ በመዋላቸው የባለስልጣኑ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዳግም ምዘገባ ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ መደረጉንም አክለዋል።
የትምህርት ዘርፍ ፍቃድ እና የፍቃድ ዕድሳት እንዲደረግላቸው ለጠየቁ ለዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ተገቢውን የጥራት መመዘኛ በማድረግ ፍቃድ መሰጠቱንም ገልጸዋል።
የአጠቃላይ የትምህርት ኢንስፔክሽን አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋፋትም የክልሎችን አቅም የማጎልበት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
ባለስልጣኑ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃዎች እውቅና ለማግኘት የሰነድና ሌሎች ዝግጅቶች እየያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ በባለስልጣኑ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል፡፡
ሪፎርሙ በትምህርት ጥራነትና አግባብነትን ላይ ተጨባጭ ውጤት ማመጣቱንና የትምህርት ኢንስፔክሽን አገልግሎት ተደራሽነት እንዲሰፋ ማስቻሉን ነው ያነሱት።
በቀጣይ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የተገልጋዮች እርካታ፣ የአካዳሚክ ጥራት ኦዲት እና በትምህርት ኢንስፔክሽን አገልግሎት ተደራሽነት ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ባለስልጣኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ በማድረግ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ ፕሮግራሞች በሀገርና በዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ማድረግና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሰው ሃይል ማፍራትን መደገፍ ይገባል ብለዋል።
ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡