ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቀነስ የሚያስችሉ የጋራ ተጨባጭ መፍትሔዎችን መተግበር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቀነስ የሚያስችሉ የጋራ ተጨባጭ መፍትሔዎችን መተግበር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቀነስ የሚያስችሉ የጋራ ተጨባጭ መፍትሔዎችን መተግበር እንደሚገባ የኮፕ 32 ተወካይ ፕሬዝደንት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የለንደን የአየር ንብረት ለውጥ የድርጊት ሳምንት ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
የኮፕ 32 ተወካይ ፕሬዝደንት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በሳምንቱ እየተሳተፉ ነው።
በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሰኔ ወር በለንደን ታይቶ የማይታወቅ የሙቀት መጠን ሊኖር እንደሚችል መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ጠቅሰዋል።
ይህም የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መከላከል እንደሚያስፈልግ ሁነኛ ትምህርት የሚያስተላልፍ መሆኑን ገልጸዋል።
እየተስተዋለ ያለው ከፍተኛ የሙቀት መጠን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጨባጭ የአየር ንብረት ለውጥ የድርጊት መርሃ ግብር ቀርጾ መተገበር የግድ መሆኑን ያስገነዘበ ነው ብለዋል።
በለንደን የአየር ንብረት ለውጥ የድርጊት ሳምንትም ለዓለም የሚበጁ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መፍትሔዎችን ማፍለቅ ከሁሉም የሚጠበቅ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የለንደን የአየር ንብረት ለውጥ የድርጊት ሳምንት እስከ ሰኔ 21 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።