ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የዘላቂ ልማት ግቦች በተግባር እየተተረጎሙ መሆናቸውን የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የዘላቂ ልማት ግቦች በተግባር እየተተረጎሙ መሆናቸውን የሚያሳይ ህያው ምስክር መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና የተቋማት ክትትል ሚኒስትር ዲኤታ አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አመራርና ሠራተኞች ጋር በመሆን በየካ ተራራ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል።


 

በዚሁ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና የተቋማት ክትትል ሚኒስትር ዲኤታ አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የዘላቂ ልማት ግቦች በተግባር እየተተረጎሙ መሆናቸውን የሚያሳይ ህያው ምስክርና ቁልፍ ማሳያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፤ በተደረገው አገራዊ ርብርብ 48 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውንና ዘንድሮም 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል።

ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በርካታ ጉዳቶችን እያስተናገደች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ ዘላቂ ዕድገትን ማረጋገጥ የሚቻለው ተፈጥሮን በመጠበቅና በመንከባከብ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

ኢትዮጵያ እያከናወነችው ባለው በዚህ መርሃ ግብር በረሃማነትና የአየር ንብረት መዛባት በጉልህ እየቀነሰ መምጣቱንም ተናግረዋል።

የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል አካሉ ካሳ በበኩላቸው በዚሁ ስፍራ ችግኞችን መትከላቸውን ገልጸው፤ አካባቢው ቀድሞ ከነበረበት መራቆት በጉልህ መለወጡን መስክረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መርሃ ግብር መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰራዊቱ ሀገር ከመጠበቅ ጎን ለጎን በዚህ አገራዊ ጥሪ ላይ አሻራውን እያሳረፈ እንደሚገኝና መርሃ ግብሩም ሰራዊቱ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠብቀው መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከቤተ መንግሥት አስተዳደር የመጣው ሀብታሙ ዮናስ በበኩሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአመት ዓመት በተሳትፎም ሆነ በሚተከሉ ችግኞች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ዘንድሮ የተያዘው አገራዊ ዕቅድ ግቡን እንዲመታ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፈችው ምናለሸዋ ማንደፍሮም የአረንጓዴ አሻራ ለትውልድ የተሻለች ሀገር የምናስተላልፍበት በመሆኑ ሁላችንም አሻራችንን ማኖር አለብን ብላለች፡፡

በተመሳሳይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፈው ተመስገን በለጠ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትልልቅ ውጤቶችን እያስገኘ መሆኑን ገልጾ የነገዋን ኢትዮጵያ የተሻለች ለማድረግ ሁሉም በጉልህ መሳተፍ እንዳለበት አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም