ቀጥታ፡

በክልሉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ ማህበራዊ እሴቶችን አሳድጓል -ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

አሶሳ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ችግሮች ከመፍታት ባለፈ የመደጋገፍ ማህበራዊ እሴቶችን ማሳደጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።




ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደገለጹት፤ በክልሉ የበጎ ፍቃድ ተግባራት በየጊዜው እያደጉ በመምጣታቸው የህዝቡን የልማትና ማህበራዊ አገልግሎቶች ለማሳለጥ እያገዙ ናቸው።

ተግባሩ የመንግስትን በጀት ከመቆጠቡ ባለፈ የህብረተሰቡን የመረዳዳት ማህበራዊ እሴት እንዲያድግ ማገዙን አስረድተዋል።

ለአብነትም በክልሉ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የቤት ግንባታ፣ የአረንጓዴ አሻራ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ እና የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ ያሳዩ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ተግባሩ የመንግስትን ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ከማሳደጉ ባለፈ አቅም ለሌላቸው ማህበረሰቦች አለኝታ መሆን እንደቻለም ተናግረዋል።

በቀጣይም ወጣቶችና የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ለማስፋት ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።




የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አለምነሽ ይባስ በበኩላቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ችግር ከማቃለል ባለፈ ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከር እና መተጋገዝ እንዲጎለብት ሚናውን ተወጥቷል ብለዋል።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱን በዘንድሮው የክረምት ወራት በማስቀጠል ከ984 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

በተግባሩ ከሚከናወኑ 14 ዋና ዋና አገልግሎቶች ውስጥ የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ አረንጓዴ አሻራና ደም ልገሳ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

በመርሀ ግብሩ ከ502 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞች እንደሚሳተፉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም