ቀጥታ፡

የመስኖ ፕሮጀክቶችን በጥራትና ፍጥነት በማጠናቀቅ የልማት አቅም ለማድረግ የስታንዳርድ አሰራሮች ስራ ላይ ውለዋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በጥራትና ፍጥነት በማጠናቀቅ የልማት አቅም ለማድረግ የሚያስችሉ የስታንዳርድ አሰራሮች ስራ ላይ ማዋሉን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ አብዱረህማን አብደላ ገለፁ።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ከክልል መስኖ ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በውስጥ ስታንዳርድ ዝግጅትና ትግበራ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ መድረክ አካሂዷል።


 

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ አብዱረህማን አብደላ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፣ አዲሱ ስታንዳርድ እያንዳንዳቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች የሚያልፉበትን ሂደት በግልጽ ያስቀምጣል።

ስታንዳርዱ በፌደራል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በክልሎችም በሚገነቡ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጭምር ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

በትግበራው አማካኝነት ትልቁ የመስኖ ፕሮጀክቶች ፈተና የሆነው የዲዛይንና ጥናት ችግር ከስር መሰረቱ እንደሚፈታ ጠቁመዋል።


 

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን መሪ ሰራ አስፈፃሚ ያሬድ ሙላት፣ ሰነዱን ሙሉ በሙሉ በውስጥ አቅም የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ስታንዳርዱ ከህዳር 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ መግባቱን አስታውቀዋል።

በዚህም በመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ ከዚህ ቀደም ይነሱ የነበሩ የጥራትና የዲዛይን ለውጥ ጥያቄዎች መስተካከሉን እና በርካታ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡


 

በመድረኩ አስተያየት የሰጡት የሲዳማ ክልል የመስኖ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን በላይ ከዚህ ቀደም ጥናቶች በሚገባ ሳይጠናቀቁ ወደ ግንባታ በመገባቱ ፕሮጀክቶች ይጓተቱ እንደነበር አስታውሰዋል።

የስታንዳርድ መዘጋጀት የትኛው ተግባር መቅደም እንዳለበት በግልጽ ስለሚያስቀምጥ ይህንን ክፍተት ሙሉ በሙሉ እንደቀረፈው ገልጸዋል።



 

የኦሮሚያ መስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር አለሙ ረጋሳ በበኩላቸው አሰራሩ ሀገር በዘርፉ የያዘችውን ትልቅ የመስኖ ልማት እቅድ በጥሩ ሁኔታ ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።


 

የአፋር ክልል መስኖና ቆላማ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኢንጂነር መሐመድ ሁማድ አሁን ላይ ስታንዳርዱ በመዘጋጀቱና ስራዎች በህግና በስርዓት መመራት በመጀመራቸው፣ ቀደም ሲል በዘርፉ ይታይ የነበረውን ተግዳሮቶችን መድፈኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም